ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት የተሳፋሪዎችን ቁጥር 50 በመቶ ቀነሰ

አዲስ አበባ፣መጋቢት 14/2012 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት አገልግሎት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የተሳፋሪዎችን ቁጥር 50 በመቶ መቀነሱን አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ስንታየሁ ወልደሚካኤል ለኢዜአ እንዳሉት የተሳፋሪዎችን ቁጥር መቀነስ ያስፈለገው የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ነው።

ከዚህ ቀደም የአንዱ የባቡር ፉርጎ በአንድ ጊዜ በአማካይ ይጭን ከነበረው 250 ሰው ከዛሬ ጀምሮ  128  ሰዎችን  ብቻ  የሚያስተናግድ ይሆናል።

የባቡር ተጠቃሚዎች ለመገልገል ሲመጡ  እጃቸውን  በውሃና  ሳሙና  እንዲታጠቡ  እንዲሁም የንፅህና መጠበቂያ አልኮልና ሳኒታይዘር እንዲጠቀሙ እየተደረገ መሆኑን ዶክተር ስንታየሁ ተናግረዋል።

የተሳፋሪዎች ሰልፍም በ1 ሜትር እንዲራራቅ የተደረገ ሲሆን የባቡር እጥረት እንዳይከሰትም ያሉት በሙሉ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ ነው።

የባቡሩ ሙሉ አካል በባለሙያዎች የኬሚካል  ርጭት እየተደረገለት  ለታሳፋሪዎች  ዝግጁ  እየተደረገ  መሆኑንም  ጠቅሰዋል።

አገልግሎቱን ሲጠቀሙ ያገኘናቸው ተሳፋሪዎች በበኩላቸው የባቡር አገልግሎቱ የኮረና ቫይረስን ለመከላከል እያደረገ ያለው ተግባር አመስግነዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም