ቀጥታ፡

ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች አቅርቦት ጋር በተያያዘ 37 የመድሃኒት መደብሮች ታሸጉ

አዲስ አበባ መጋቢት 14/2012 (አዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ ለኮሮና ቫይረስ መከላከል የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች አቅርቦት ጋር በተያያዘ የተለያየ ጥፋት የፈጸሙ 37 የመድሃኒት መደብሮች እንዲታሸጉ መደረጉ ተገለጸ።

የመድሃኒት መደብሮቹ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚረዱ ቁሳቁሶችን በተጋነነ ዋጋ በማቅረብ፣ ምንጩ ያልታወቀ ምርት በመሸጥና ምርቱ እያለ የለም ሲሉ የነበሩ መሆናቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምግብ፣ መድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ጉዳዩን አስመልክቶ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምግብ፣ መድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ደብረወርቅ ጌታቸው እንደገለጹት፤ በከተማው ውስጥ ከሚገኙ 940 የመድሃኒት መደብሮች መካከል በ725ቱ ላይ ቁጥጥር ተደርጓል።

በተደረገው ቁጥጥር የተጋነነ ዋጋ ያቀረቡ፣ ምንጩ ያልታወቀ ምርት የሸጡና ምርቱ እያላቸው 'የለም' ሲሉ በነበሩ 37 የመድሃኒት መደብሮች ላይ የማሸግ ርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።

ከነዚህ በተጨማሪ 25 የመድሃኒት መደብሮች በማስጠንቀቂያ መታለፋቸውን ጠቁመዋል።

ሁለት የሳሙናና የዲተርጀንት አቅራቢነት ፈቃድ ያላቸው ግለሰቦች 'የእጅ ማጽጃ ኬሚካል (ሳኒታይዘር) እና የእጅ ሳሙና እናመርታለን' በሚል ሲያታልሉ በመገኘታቸው በቁጥጥር ስር እንደዋሉ አቶ ደብረወርቅ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ተመሳሳይ ድርጊት በመፈጸም የተጠረጠሩ ግለሰቦች መኖራቸውን ገልጸዋል።

የተጀመረው የቁጥጥር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያስገነዘቡት ምክትል ዋና ዳይሬክተር፤ ምርቶቹን ተደራሽ ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም