በሀዋሳ ጭፈራ ቤቶች እንዲዘጉና ዋጋ የጨመሩ የንግድ ተቋማት እንዲታሸጉ ተደረገ

ሀዋሳ ኢዜአ መጋቢት 14/2012 (ኢዜአ) በሀዋሳ ከተማ የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል የምሽት ጭፈራ ቤቶች እንዲዘጉና ያልተገባ ዋጋ የጨመሩ የንግድ ተቋማት እንዲታሸጉ መደረጉን የከተማዋ ንግድና ገበያ ልማት መምሪ ገለጸ፡፡

ህብረተሰቡም የመከላከያ መንገዶችን በመጠቀም አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ እየተሰራ መሆኑም ተመልክቷል።

የከተማዋ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሽታዬ ጫቡላ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት የምሽት ጭፈራ ፣ የሺሻና ጫት ማስቃሚያ ቤቶች በርካታ ሰዎች የሚገኙባቸው በመሆኑ ለቫይረሱ ስርጭት የሚያደርጉት አስተዋፅኦ የጎላ ነው፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ከወር በፊት የጀመረውን የሺሻና ጫት ቤቶችን የማሸግ ሥራውን አጠናክሮ መቀጠሉን ጠቅሰዋል።

ከመጋቢት 13/2012ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ የምሽት ጭፈራ ቤቶች እንዲዘጉ መደረጉንና ይህንንም የሚቆጣጠር የፀጥታ ኃይል መመቻቸቱን ገልጸዋል፡፡

ነጭ ሽንኩርት፣ ሎሚና ሌሎች ምርቶች በተለይም በንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ላይ አለአግባብ የዋጋ ጭማሪ አድርገው የተገኙ 78 የንግድ ተቋማት እንዲታሸጉ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡

የከተማዋ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጎሳዬ ጎዳና በበኩላቸው ዜጎች ስለ ቫይረሱ ስርጭትና መከላከያ መንገዶች በቂ እውቀት እንዲኖራቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች  በአውቶብስ መናኸሪያዎች እየተካሄዱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በነዚህ ሥፍራዎች ከትራንስፖርት ማህበራትና ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ጋር በመተባበርም የእጅ መታጠቢያዎችን ተዘጋጅተዋል ብለዋል።

የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሰራተኞችን የሚያመላልሱ አውቶብሶች ብዛት ስላላቸው ንፅህና ከመጠበቅ ባሻገር ትርፍ እንዳይጭኑና ከማሳፈራቸው በፊት እጃቸውን እንዲታጠቡ  እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በኮንትራት ሰበብ ያለበቂ ምክንያት የሚቆሙ፣ ትርፍ የሚጭኑ እንዲሁም ከታሪፍ በላይ የሚያስከፍሉ ተሸከርካሪዎች ላይ አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀታቸውንም አስታውቀዋል፡፡

ቫይረሱ በኢትዮጵያ መከሰቱ ከተነገረበት ዕለት ጀምሮ ህብረተሰቡ የመከላከያ መንገዶችን በመጠቀም አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲደርግ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራታ እየተከናወኑ መሆኑን የገለጹት ደግሞ  የሀዋሳ ከተማ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ቡሪሶ ቡላሾ ናቸው።

በተለይ ከውጭ ዜጎችና ከኢንዱስትሩ ፓርክ ሰራተኞች ጋር በተያያዘ አልፎ አልፎ የማግለል አዝማሚያዎች እንደሚስተዋሉ የተናገሩት አቶ ቡሪሶ "በዚህ ረገድ ህብረተሰቡን እያስተማርን ነው" ብለዋል፡፡

እስካሁን ቫይረሱ በሀዋሳ ከተማ እንዳልተከሰተ ገልጸው ከዚህ ጋር በተያያዘ ማንኛውንም አዲስ መረጃ  ለህብረተሰቡ ግልጽ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።

በሽታውን በተቀናጀ አግባብ ለመከላከል ቀደም ሲል በከተማዋ ምክትል ከንቲባ አስተባባሪነት ግብረ-ኃይል መቋቋሙ ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም