በአዋሽ የሺሻ መጠቀሚያዎች እንዲወገዱና ጫት ማስቀሚያ ቤቶች እንዲታሸጉ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በአዋሽ የሺሻ መጠቀሚያዎች እንዲወገዱና ጫት ማስቀሚያ ቤቶች እንዲታሸጉ ተደረገ
መጋቢት 13/2012 (ኢዜአ) በአፋር ክልል አዋሽ ሰባት ኪሎ ከተማ ከ100 በላይ የሺሻ መጠቀሚያ እቃዎችን እንዲወገዱና 11 መጠጥ ቤቶች እንዲታሸጉ መደረጉን የከተማዋ አስተዳደር ከንቲባ አስታወቁ።
ከንቲባው አቶ ኢብራሂም መሃመድ እንደገለጹት ከተማዋ ከጀቡቲና ከምስራቅ ኢትዮጵያ ጋር የሚያገናኝ ዋነኛ መተላለፊያ መንገድ በመሆኗ ከፍተኛ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ታስተናግዳለች።
በነዚህና ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች በሀገሪቱ የተከተሰው የኮሮና ቫይረስ ከሚያሰጋቸው ከተሞች አዋሽ ሰባት ኪሎ አንዷ ናት።
አስተዳደሩ ይህን ከግምት በማስገባት በከተማው የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል የሚረዱ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የተለያዩ የቅድመ-ጥንቃቄ ስራዎች እያከናወነ ይገኛል።
ከነዚህም በከተማዋ ለቫይረሱ ሊያጋልጡ የሚችሉ ከ100 በላይ የሺሺ መጠቀሚያ እቃዎች እንዲቃጠሉ መደረጉን ከንቲባው አስታውቀዋል።
11 የጫት ንግድ ቤቶች ደግሞ ለቫይረሱ በሚያጋልጥ ሁኔታ ሰዎች ሰብስበው ሲያስቅሙ ተደርሶባቸው መታሸጋቸውንና እርምጃው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል
የጥንቃቄ ስራዎች እያከናወኑ ያሉት ከሚመለከታቸው የጤናና ጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር እንደሆነም ተናግረዋል።
በተጨማሪም የእንግዳ ማረፊያ ሆቴሎች ለደንበኞቻቸው ተገቢውን የንጽህና አገልግሎት እንዲያሟሉ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው አንድ መጠጥ ቤት መታሸጉንም አስረድተዋል።
ከንቲባው እንዳሉት በከተማዋ የተለያዩ የሸቀጥ እቃዎችና መድኃኒቶች በተለይም የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ላይ ተገቢ ያልሆነ ዋጋ እንዳይጨምሩ ቁጥጥር እየተደረገ ነው።
ከ200 በላይ በጎ-ፍቃደኛ ወጣቶች በከተማዋ የሰዎች እንቅስቃሴ በሚበዛባቸው አካባቢዎች የእጅ ማስታጠብ በማመቻቸት የቫይረሱ ስለመተላለፊያ መንገዶችና መከላከያው ትምህርት እየሰጡ እንደሚገኙም አስረድተዋል።