ቀጥታ፡

ከየትኛውም አገር ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ መንገደኞች ከነገ ጀምሮ በራሳቸው ወጪ በሆቴል ይቆያሉ

መጋቢት 13/2012 ከየትኛውም የውጭ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ መንገደኞች በሙሉ ከነገ ጀምሮ በራሳቸው ወጪ በሆቴል ተለይተው ለ14 ቀናት ይቆያሉ።

ዲፕሎማቶች በየአገራቸው ኤምባሲዎች እራሳቸውን ለ14 ቀናት ለይተው የሚያቆዩ ሲሆን የትራንዚት በረራ መንገደኞችም የትራንዚት በረራቸውን እስኪያገኙ በስካይላይት ሆቴል ተለይተው ይቆያሉ ተብሏል።

ማናቸውም የውጭ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ መንገደኞች በሆቴል ተለይተው ለ14 ቀናት እንዲያቆዩ የሚያስገድደው ውሳኔ ከእሁድ እኩለ ሌሊት ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል።

በመሆኑም ሰኞ ጠዋት የሚገቡ ሁሉም መንገደኞች በስካይ ላይት ወይም በጊዮን ሆቴል በራሳቸው ወጪ ተለይተው የሚቆዩ መሆኑ ታውቋል።

የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዛሬ እንዳስታወቁት በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 11 ደርሷል።

ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሁለቱም ኢትዮጵያኖች ሲሆኑ አንደኛው የ28 ዓመት ወጣት ቫይረሱ መኖሩን ሪፖርት ካደረጉ አገራት ተጉዞ የነበረ መሆኑ ተገልጿል።

ወጣቱ ቤልጂየምና ኔዘርላንድ ተጉዞ የነበረና መጋቢት 5 ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰ ሲሆን ተማሚው ኢትዮጵያ ከገበበት ጊዜ አንስቶ ራሱን ለይቶ ማቆየቱም ተመልክቷል።

ሁለተኛው ግለሰብ ደግሞ 34 ዓመት ኢትዮጵያዊ ሲሆን ከዱባይ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በተደረገለት ምርመራ የሙቀት ምልክት በማሳየቱ በለይቶ ማቆያ ቆይቶ በቫይረሱ መያዙ ተረጋግጧል።

ሁለቱም ቫይረሱ የተገኘባቸው ግለሰቦች በጥሩ የጤንነት ሁኔታ ላይ የሚገኙ መሆኑን የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት አስታውቀዋል።

ከዚህ በፊትም ቫይረሱ ከተገኘባቸው ዘጠኝ ግለሰቦችም የ8ቱ ጤንነት በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆኑ ተገልፇል።

በኢትዮጵያ እስካሁን 392 ናሙናዎች የቫይረሱ ምርምራ የተደረገ ሲሆን ከግለሰቦቹ ጋር ንክኪ የነበራቸው ሰዎች ክትትል እየተደረገ መሆኑም ተገልጿል።

የኮሮና ቫይሰር በአፍሪካ እስካሁን በ40 አገራት ላይ መከሰቱ የተረጋገጠ ሲሆን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም 1 ሺህ 114 ደርሷል።

በአህጉሪቱ የሟቾች ቁጥርም 28 መድረሱን የአፍሪካ በሽታ መከላከያና መቆጣጠሪያ ማእከል አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም