የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በምስራቅ ሸዋ ዞን የልማት ክላስተሮችን ጎበኙ

58

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 12/2012 (ኢዜአ) የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሣና ሌሎች የስራ ኃላፊዎች በምስራቅ ሸዋ ዞን የተለያዩ የልማት ክላስተሮችን ጎበኙ። 

የስራ ኃላፊዎቹ በመስኖ የለማ የቆላ ስንዴ ማሳ፣ በወጣቶች  እየለማ የሚገኘውን  የአቮካዶ  ችግኝ እንዲሁም  በአደአ ወረዳ በአረንጓዴ  የአሻራ ቀን  በ105 ሄክታር  መሬት ላይ ተተክሎ የነበረን የአቮካዶ ክለስተር ጎብኝተዋል።

የልማት ክላስተሮቹ በበሶት፣ በአዳማ እና በአደአ ወረዳዎች የሚገኙ ናቸው።

የክልሉ ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሣ በቀደመው ጊዜ ግብርናው ላይ ከንግግር ያለፈ በተግባር ብዙ ተሰርቷል ማለት እንደማይቻል ተናግረዋል።

ይሁንና በብልጽግና ዘመን ግብርናውን በማዘመንና አርሶ አደሩን ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ እየተሰራ ይገኛልም ብለዋል፡፡

በዚህም በክልሉም 126 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ በመስኖ እየለማ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም የክልሉ መንግስት ለአርሶ አደሮቹ ግብዓቶችን በማቅረብና ቀደም ሲል የነበረውን 'ስንዴ በቆላማ አካባቢ አይለማም' የሚለውን ብሂል በማስቀረት እንዲለማ በማስቻል በተግባር እያሳየን ነው ብለዋል፡፡

የክልሉ የግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ በበኩላቸው ስንዴን አገር ውስጥ በመስኖ በማልማት ከውጭ የሚገባውን ምርት ለማስቆም እንሰራለን ብለዋል፡፡

በቆላማ አካባቢ ስንዴን በመስኖ የሚያለሙ አርሶ አደሮች ከዚህ ቀደም ስንዴን በእርዳታ እንጂ በምርት እንደማያውቁት ተናግረዋል፡፡

መንግስት ባደረገላቸው ድጋፍ ከ1 ሄክታር ከ50 እስከ 60 ኩንታል ስንዴ ለመሰብሰብ መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም