ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያስችል ግብረ-ኃይል አዋቀረች

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 12/2012 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የኮሮናን ቫይረስ መከላከል የሚያስችል ግበረ-ኃይል ማዋቀሯን አስታወቀች።

ቤተክርስቲያኗ ከመደበኛው የስብከተ ወንጌል ጉባኤ ውጭ ያሉ ስብሰባዎችና መንፈሳዊ ጉዞዎች ለጥቂት ቀናት እንዳይደረጉም ትዕዛዝ አስተላልፋለች።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጠችው ቤተክርስቲያኗ በውጭ አገር ዜጎች ላይ የሚደረገውን ማግለል እንደምታወግዝም አስታውቃለች። 

የቤተክርስቲያኗ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊና የምስራቅ ጉጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዩሴፍ ቅድስት ቤተክርስቲያን ፀሎትና ምሕላ ከማድረግ ባሻገር ጤነኞችን የመጠበቅና ሕሙማንን የማጽናናት ኃላፊነት አለባት ብለዋል።

በመሆኑም ቋሚ ሲኖዶሱ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ጀምሮ በየደረጃው ከሊቃውንት ቤተክርስቲያንና ከጤና ባለሙያዎች የተውጣጣ ግብረ ኃይል አቋቁሟል።

ግብረ ኃይሉ በጠቅላይ ቤተ-ክህነት ስር የሚሰራ ሲሆን ከሚመለከታቸው የመንግስት መስሪያ ቤቶች ጋር በመተባበር መረጃዎችን እንደሚያሰናዳ ነው የተገለፀው።

ቤተክርስቲያኗ አለመጨባበጥ ፣ እጅን በሚገባ መታጠብና ሳይጠጋጉ ዘርዘር ብሎ የመቆም ተግባራት ከቀኖናዋ ጋር የማይጋጩ በመሆናቸው ምዕምናን ይተግብሩት ብላለች።

በተጨማሪም ምእመናን በቅዳሴና በምሕላ ፀሎት ጊዜ በውስጥም ሆነ በአፀደ ቤተክርስቲያን ዘርዘር ብሎ በመቆም በሽታውን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዙ ብለዋል።

ሊቃውንት፣ መምህራን፣ ካሕናት፣ ሰባኪያነ ወንጌልና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ከተሳሳቱ መረጃዎች ተቆጥበው የቤተክርስቲያኗን መመሪያዎች በየአጥቢያቸው እንዲያስፈጽሙም ጠይቀዋል።

በሽታው በዓለም ላይ የመጣ በመሆኑ በጋራ ቫይረሱን ከመከላከል ውጭ በማንኛውም ዜጋ ላይ አላስፈላጊ ማግለል እንዳይፈፀምም ጥሪዋን ታቀርባለች ብለዋል።

ከዚህ ጎን ለጎንም የሚመለከታቸው የጤና ተቋማት ቤተክርስቲያኗ ለምታደርጋቸው እንቅስቃሴዎች አስፈላጊውን ትብብር ያድርጉ ሲሉም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም