በማዕከላዊና ምዕራባዊ ጎንደር ኮሮናን ለመከላከል ግብረ ኃይልና የለይቶ ማቆያ ተመቻቸ - ኢዜአ አማርኛ
በማዕከላዊና ምዕራባዊ ጎንደር ኮሮናን ለመከላከል ግብረ ኃይልና የለይቶ ማቆያ ተመቻቸ
ጎንደር/ ነቀምቴ መጋቢት 12/2012 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ማዕከላዊና ምዕራባዊ ጎንደር ዞኖች የኮሮና በሽታን ለመከላከል ግብረ ኃይል መቋቋሙንና የተጠርጣሪዎች ለይቶ ማቆያ መመቻቸቱ ተገለጸ።
በኦሮሚያ ክልል ነቀምቴ ከተማ ደግሞ በሽታውን ለመከላከል የሚያግዙ የቁሳቁስ አቅርቦት ችግር እንዳጋጠማቸው ነዋሪዎች ተናገሩ።
በማዕከላዊ ጎንደር 15 ወረዳዎች ለተውጣጡ የጤና ጽህፈት ቤት አካላት ስለ በሽታው መከላከል የተሰጣቸው ስልጠና ዛሬ ሲጠናቀቅ የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ደረሰኝ ፈንቴ እንደተናገሩት ህብረተሰቡን ከቫይረሱ ለመጠበቅ ባለድርሻ አካላትን ያካተተ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል።
ግብረ ኃይሉን እስከ ወረዳ ድረስ በማውረድ በግንዛቤ ማስጨበጫ፣ የመከላከያ ዘዴዎችን በመተግበር፣ በመረጃ ቅብብሎሽ ተጠርጣሪዎችን በለይቶ ማቆያ እንዲታከሙ ለማስቻል ጥረት እየተደረገ ነው።
በአሁኑ ወቅትም በጎንደር ከተማ፣ በጭልጋና በታች አርማጭሆ ወረዳዎች በሚገኙ ሆስፒታሎች ሶስት የለይቶ ማቆያ ማዕከላት ተመቻችተው የሰው ኃይልና ቁሳቁስ እየተሟላላቸው ይገኛል ብለዋል።
በቀጣይም በሰባት የገጠር ሆስፒታሎች የለይቶ ማቆያ ማዕከላቱን በማቋቋም ለአገልግሎት እየተዘጋጁ መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
በማክሰኝት ከተማ ለሁለት ቀናት በተሰጠው ስልጠና ከ45 በላይ የጤና ባለሙያዎችና የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡
በሌላ በኩል በምዕራብ ጎንደር ዞን ከሱዳን ጋር በሚያዋስኑ የድንበር ከተሞች የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል የሙቀት ልኬት ምርመራ መጀመሩንና የተጠርጣሪዎች የለይቶ ማቆያ መመቻቸቱ ተገልጿል፡፡
በዞኑ ማህበራዊ ልማት መምሪያ የጤና ክትትል ዋና የሥራ ሂደት ቡድን መሪ አቶ ብርኃኑ መንገሻ እንዳሉት በሱዳን አዋሳኝ በሚገኙ የመተማ ዮሃንስና ገለባት ከተሞ የሰዎች እንቅስቃሴ ገደብ እንዲኖረው ተደርጓል።
ህብረተሰቡ ከአላስፈላጊ ንክኪና መዘናጋት እንዲቆጠብ የማስተማር ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የከባድ ተሸከርካሪ ሾፌሮችና ሌሎች ሰዎች በኬላ የሙቀት ልኬት ቁጥጥር ተጀምሯል ነው ያሉት።
ተጠርጣሪዎችን ተለይቶ የሚቆይበት ቦታ በመተማ ሆስፒታል መዘጋጀቱን ጠቅሰው ፤ ባለፉት ሁለት ቀናትም 400 የሚሆኑ ሰዎችን ሙቀት መለካት መቻሉንና እስካሁንም ተጠርጣሪ አለመገኘቱን አስታውቀዋል።
የቅድመ መከላከያ ቁሳቁሶችን ለማሟላት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
የመተማ ዮሃንስ ከተማ ነዋሪ አቶ ደሴ በለጠ በሰጡት አስተያየት በመተማና ገለባት መካከል ይደረግ የነበረው ልቅ የሆነ እንቅስቃሴ መገደቡ የነበረባቸው ስጋት እንደቀነሰላቸው ተናግረዋል፡፡
በተለያዩ ስራዎች ሱዳን ቆይተው የሚመጡ የቀን ሰራተኞች በጫካ የሚገቡ በመኖራቸው ተገቢው ክትትል እንዲደረግ ጠቁመዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያግዙ የቁሳቁሶች አቅርቦት ችግር እንደገጠማቸው የነቀምቴ ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የከተማው ቀበሌ ስድስት ነዋሪ አቶ ሀብቴ ጥበቡ እንዳሉት አልኮልና ሌላም ቁሳቁስ ለመግዛት በየመድኃኒት ቤቶች ቢዞሩም ማግኘት አልቻሉም ፡፡
ለበሽታው መከላከያ አስፈላጊ ናቸው ተብለው በጤና ባለሙያዎችና በመገናኛ ብዙሃን የሰሙት ቁሳቁስ አቅርቦት ባለመኖሩ መቸገራቸውን የተናገሩት ደግሞ ሌላው የከተማው ቀበሌ ሶስት ነዋሪ አቶ ኤቢሣ ጉያሣ ናቸው።
የነቀምቴ ከተማ የጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ አመያ በከተማው በሽታውን ለመከላከል የቁሳቁስ እጥረት ቢያጋጥምም ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫና በሁሉም የመንግሥት መስሪያ ቤቶች የእጅ መታጠብ ፕሮግራም መጀመሩን ገልጸዋል።
የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ሪፌራል ሆስፒታል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ተመስገን ጥላሁን በበኩላቸው በሆስፒታሉ የአልኮል ችግር እንደሌለ ተናግረዋል።
በበሽታው የተጠረጠሩ ሰዎች የሚቆዩበት በሆስፒታሉ መዘጋጀቱን አመልክተው፤ ለአራቱ የወለጋ ዞኖች የሚያገለግልና 20 አልጋዎች ያሉት የተጠርጣሪዎች ማቆያ ቦታ ከየዞኑ የጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤቶች ጋር በመተባበር ማዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል፡፡