ቀጥታ፡

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የኮሮናን ቫይረሰ ለመከላከል ግብረ ኃይል አቋቁመው እየሰሩ ነው

መጋቢት 12/2012 ኢዜአ የኮሮናን ቫይረስ ለመከላከል ግብረ ኃይል አቋቁመው እየሰሩ መሆኑን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተወካዮች ገለጹ።

የአዳማ፣ የወለጋና የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲዎች ተወካዮች ቫይረሱን አስቀድሞ ለመከላከል በከፍተኛ ኃላፊዎች የሚመራ ግብረ ኃይል አቋቁመው እየሰሩ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል። 

የአዳማ ዩኒቨርሲቲ የዓለምአቀፍ ግንኙነትና የኮርፖሬት ኮሙኑኬሽን ዳይሬክተር ዶክተር ካሳዬ ጉተማ እንዳሉት በዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች የሚመራና ከተማሪዎች፣ ከመምህራንና ከአስተዳደር ሰራተኞች የተውጣጣ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ስራ ገብቷል።

የገጽ ለገጽ ትምህርት በመቋረጡ ለተማሪዎች የኦንላይን ትምህርት በማመቻቸት፣ የንጽህና መጠበቂያዎችን በማቅረብና ስለ ቫይረሱ በማስገንዘብ የቅርብ ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል።

ግብረ ኃይሉ ወደ ስራ ከገባ በኋላ ተማሪዎች የትምህርት ጊዜያቸው እንዳይስተጓጎል 450 ኮርሶችን በኦን ላይ እንዲከታታሉ የማድረግ ስራም ተሰርቷል ነው ያሉት።

በሚኒ ሚዲያ፣ በብሮሸርና ባነር በመለጠፍ አስተማሪ መልዕክቶች ለተማሪዎች፣ ለመምህራንና ለአካባቢው ነዋሪዎች ጭምር እየተላለፈ መሆኑንም አክለዋል።

የወለጋ ዩኒቨርሲቲ የኮርፖሬት ኮሙኑኬሽን ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ደሳለኝ በበኩላቸው እንደገለጹት በዩኒቨርሲቲው የባለሙያዎች፣ የቴክኒክና የአቅርቦት ስራ የሚሰራ ግብረ ኃይል ተቋቁሟል።

ለተማሪዎች የስነ-አዕምሮ ባለሙያ በመመደብ ስለ ቫይረሱ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸውም እየተደረገ ነው።

ግብረ ኃይሉ በማኅበረሰብ ራዲዮ ለተማሪዎች ስለ ቫይረሱ ጠቃሚ መልዕክቶች እንዲተላለፉ እያደረገ እንደሆነና የጽዳት መጠበቂያዎች ተገዝተው እየተሰጡ መሆኑን ገልጸዋል።

በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲም ከሃይማኖት አባቶች፣ ከአካባቢው ማኅበረሰብና ከዞኑ መስተዳድር ጋር በመሆን ለተማሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ መካሄዱን የውጭና የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ አቶ የወንድ ወሰን ሞላ ተናግረዋል።

ከመንግስትና ከኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሚተላለፉ መረጃዎችን በበራሪ ወረቀትና በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች እንዲያገኙም እየተደረገ ነው።

ለጊዜው የተቋረጠውን የገጽ ለገጽ ትምህርት ለማካካስ ተማሪዎች በመኝታ ክፍላቸው ሆነው የሚሰሯቸው አሳይመንቶችና ተዛማጅ የትምህርት መርጃዎች እየተታደሉ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ዕለት በዕለት የሚማሩት ትምህርት በወረቀት ቅጂ እንዲደርሳቸው እየተደረገ እንደሆነም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም