በዋና ዋና የክልል ከተሞች የኮሮና ቫይረስ ምርምራ ሊጀመር ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዋና ዋና የክልል ከተሞች የኮሮና ቫይረስ ምርምራ ሊጀመር ነው
አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 12/2012 ( ኢዜአ) በአገሪቷ ዋና ዋና የክልል ከተሞች የኮሮና ቫይረስ ምርምራ ሊጀመር መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የኮሮና ቫይረስ ምልክቶች የሚታይባቸው ሰዎች የሚደውሉባቸው አማራጭ የስልክ ቁጥሮችም ይጨመራሉ ብሏል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሳህረላ አብዱላሂ እስካሁን የኮሮና ቫይረስ ምርመራ የሚካሄደው በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ብቻ እንደሆነ አውስተዋል።
ሆኖም ምርመራውን በዋና ዋና የክልል ከተሞችም ማድረግ እንዲቻል የዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።
"ባህር ዳር፣ ሃዋሳ፣ መቐለና አዳማ የኮሮና ቫይረስ ምርምራ ከሚደረግባቸው ከተሞች መካከል በዋነኝነት የሚጠቀሱ ናቸው" ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታዋ።
በክልሎች ምርመራ የማድረግ ፍላጎት ቢኖርም በአገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ የመመርመሪያ ኪቶች እጥረት በኢንስቲትዩቱ ብቻ እንዲገደብ አድርጎት መቆየቱን ገልጸዋል።
ከቻይና መንግስትና ከአፍሪካ ሕብረት የበሽታ መቆጣጠርና መከላከል ማዕከል የምርመራ ኪት ድጋፍ መገኘቱንና ምርመራ በሚካሄድባቸው ከተሞች እንደሚሰራጭም ተናግረዋል።
የኢዜአ ሪፖርተር በከተሞቹ ምርመራው መቼ ይጀመራል? ሲል ላቀረበው ጥያቄ "ትክክለኛው ቀን ባይታወቅም ምርመራው በቅርብ ጊዜ ይጀመራል" ሲሉ ወይዘሮ ሳህረላ ምላሽ ሰጥተዋል።
የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በሁሉም ክልሎች የለይቶ ማቆያ እንዲዘጋጅ መደረጉንና በክልል ምክትል ፕሬዚዳንቶች የሚመራ ግብረ ኃይል መቋቋሙን ተናግረዋል።
በመግቢያና መውጫ ኬላዎች ዋና ዋና የሚባሉ የአውሮፕላን መዳረሻዎችና ባቡር የሚተላለፍባቸው መንገዶች ላይ ምርመራው መጀመሩን ገልጸዋል።
ጤና ሚኒስቴር ክልሎች ቫይረሱን ለመከላከል የሚጠይቁትን ቁሳቁስና ግብዓት እያቀረበ እንደሆነም አክለዋል።
ስለ ኮሮና ቫይረስ መረጃ ለማግኘት 952 እና 8335 እንዲሁም 0112765340 የስልክ መስመሮችን ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ እነዚህ በቂ ባለመሆናቸው አማራጭ መስመሮች ይዘጋጃሉ ብለዋል።
በአዲስ አበባ ያሉ ሁሉም ሆስፒታሎቻችን ቢያንስ ለይቶ ማቆያ ክፍሎችን እንዲያዘጋጁ መደረጉን ገልጸው ፤ ህብረተሰቡ የቫይረሱ ምልክት ከታየበት ወደ ተቋማቱ እንዲሄድም ጥቆማዎችን እየሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አማራጭ ስልክ ቁጥሮችንም ለመተግበር ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር እየተነጋገሩ መሆኑንም ገልጸዋል።
የክልል ጤና ቢሮዎችም አማራጭ የስልክ መስመሮችን ማዘጋጀታቸውንና ይህም ተግባር ቀጣይነት እንደሚኖረው አስታውቀዋል።
በኮሮና ቫይረስ አሳሳቢነት የተነሳ የኔትወርክ ችግር ያለባቸውን አካባቢዎች የአገልግሎቱ ተደራሽ ለማድረግ ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር በመነጋገር መፍትሄ ለማበጀት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አክለዋል።