በጋምቤላ ከተማ ተገቢ ያልሆነ ዋጋ በጨመሩ የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰድ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ከተማ ተገቢ ያልሆነ ዋጋ በጨመሩ የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰድ ተጀመረ
መጋቢት 12/2012 ኢዜአ በጋምቤላ ከተማ የኮሮና ቫይረስን ሰበብ በማድረግ በምግብና ሌሎች ሸቀጦች ላይ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ የንግድ ተቋማትን በመለየት ህጋዊ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን የከተማው ንግድና ኢንዱስትሪ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ የማነ ተስፋዬ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት እርምጃ መውሰድ የተጀመረው በምግብ ፣ንጽህና መጠበቂያ፣ ነጭ ሽንኩርትና ሌሎች ፍጆታ ሸቀጦች ዋጋ በጨመሩ ተቋማት ላይ ነው።
በከተማው ከመጋቢት 10/2012ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ዛሬ በተደረገው ክትትል የተለዩ 27 የንግድ ተቋማት መታሸጋቸውን ጠቁመው" በቀጣይ እርምጃው ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል" ብለዋል።
ከታሸጉት የንግድ ተቋማት መካከል የእህል መጋዝኖች፣ ወፍጮ ቤቶች፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ሱቆችና ፣ ሱፐር ማርኬቶች ይገኙበታል።
እርምጃ የተወሰደባቸው የንግድ ተቋማት በህግ እንዲጠየቁ ጭምር እየተሰራ መሆኑን ኃላፊው አስታውቀዋል።
ጽህፈት ቤት በተለይም የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል በሚደረገውን ጥረት የጽዳት መጠበቂያና ሌሎች ምርቶች ላይ እጥረት እንዳይከሰት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተካተቱበት ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በአቋራጭ ለመክበር የሚሞክሩ አካላትን ህብረተሰቡ በማጋለጥ የጀመረውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥልም የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።