በሀዋሳ የውሀ አገልግሎት መቆራረጥ የኮሮና ቫይረስ የመከላከሉ ስራ አስቸጋሪ እያደረገው ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሀዋሳ የውሀ አገልግሎት መቆራረጥ የኮሮና ቫይረስ የመከላከሉ ስራ አስቸጋሪ እያደረገው ነው
መጋቢት 12/2012 ሀዋሳ (ኢዜአ) በሀዋሳ ከተማ የሚታየው የውኃ ችግር የግል ንፅህናን በመጠበቅ ከኮሮና ቫይረስ ተጋላጭነት ለመከላከል የሚደረገው ጥረት አስቸጋሪ እንዳደረገው አስተያየታቸውን የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ገለፁ ፡፡
የነዋሪዎች ቅሬታ በተመለከተ የተጠየቀው የከተማ አስተዳደሩ በበኩሉ ቅሬታው አግባብነት ያለው በመሆኑ ለመፍታትና ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት እየተሰራ ነው ብሏል፡፡
በከተማው የንጹህ የመጠጥ ውሃ እጥረት መታየት ከጀመረ ሰንበትበት ማለቱን ወይዘሮ ታርኳ ዮሐንስ የተባሉ ነዋሪ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ እጥረቱ እየተባባሰ መጥቶ በሳምንት አንድ ቀን ለዚያውም ሌሊት ስለሚመጣ ወረፋ በመጠበቅ እየተቸገሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
እጅን በሳሙና በመታጠብ የኮሮና ቫይረስን መከላከል እንደሚቻል ቢነገረንም ተግባራዊ ለማድረግ ውሃ አለመኖሩ ተጋላጭ እንዳያደርጋቸው ስጋታቸውን ገልጸው የሚመለከተው አካል አፋጣኝ መፍትሄ መስጠት አለበት ነው ያሉት፡፡
አቶ ዝናቡ አብርሃም የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው የግል ንጽህናቸውን ለመጠበቅና የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል በከተማዋ የገጠመው የውሃ እጥረት ስጋት ውስጥ ጥሎአቸዋል ።
ያለ ውሃ ስለንጽህና ማሰብ ከባድ ነው ያለው አስተያየት ሰጪው ጊዜው አጣዳፊ በመሆኑ ነዋሪውን ስጋት ላይ የጣለውን የውሃ እጥረት ለመፍታት መንግስት አማራጭ መንገዶችን መፈለግ አለበት ብለዋል።
የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር ውሃና ፈሳሽ አገልግሎት ድርጅት ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ደምሴ ዳንኤል በበኩላቸው ካለፈው አንድ ወር ጀምሮ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር መከሰቱን አምነዋል፡፡
የውሀ እጥረት የለም ነገር ግን የከተማው ውሃ ከሌላ አካባቢ የሚመጣ ሆኖ በተደጋጋሚ በሚከሰተው የመብራት መቆራረጥ ምክንያት ችግሩ ሊባባስ እንደቻለ አስረድተዋል ።
በቀጣይ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ለከተማ ውሃ ራሱን የቻለ የኤሌክትሪክ መስመር እንዲዘረጋ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ በመፈጸም በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የነዋሪውን ቅሬታ በተመለከተ የተጠየቁት የሐዋሳ ከተማ ምክትል ካንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው ቅሬታው ትክክል መሆኑን አምነው ችግሩ የተፈጠረው በመብራት መቆራረጥ ምክንያት ነው ብለዋል፡፡
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የከተማ አስተዳደሩ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ደቡብ ሪጂን ጋር ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አመላክተዋል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ደቡብ ሪጅን የሚመለከተውን አካል ለማነጋገር ሪፖርተሩ ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ መስክ ላይ ናቸው በሚል ሰበብ ሊሳካ አልቻለም።