ሆቴሎች ለሠራተኞቻቸው የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ እንዲያሟሉ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ሆቴሎች ለሠራተኞቻቸው የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ እንዲያሟሉ ጥሪ ቀረበ
መጋቢት 12/2012 ኢዜአ ሆቴሎች ለሚያሠሯቸው ባለሙያዎች የንጽህና መጠበቂያዎችን በማቅረብ የኮሮናን ቫይረስ እንዲከላከሉ የኢትዮጵያ ሆቴል ባለሙያዎች ማኅበር ጥሪ አቀረበ።
ማኅበሩ የኮሮናን ቫይረስ ለመከላከል የሚሠራቸውን ሥራዎች አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
የማኅበሩ የቦርድ አባል አቶ ይታሰብ ስዩም የሆቴል ባለሙያዎች እንደ ጤና ባለሙያዎች ሁሉ ከውጭ አገራት ከሚገቡ ዜጎች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
ይህም ከፍተኛ ጥንቃቄ ካልተደረገ የኮሮና ቫይረስ እንዲዛመት ሊያደርግ ስለሚችል የሆቴል ባለንብረቶች የንጽህና መጠበቂያዎችን ለሠራተኞቻቸው በማቅረብ ኃላፊታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ማኅበሩ ባደረገው ግምገማ በአንዳንድ ሆቴሎች የንጽህና መጠበቂያዎች እየቀረቡ አለመሆኑን መለየቱን ገልጸው፣ ሆቴሎች ተጨማሪ በጀት በመያዝ እንዲያሟሉ ግፊት እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
የባለሙያዎች ጤናና ንጽህና ካልተጠበቀ ቫይረሱ በቀላሉ ወደ አገልግሎት ተቀባዩ እንዲሁም ወደ ማኅበረሰቡ የመሰራጨት ዕድሉ ሰፊ በመሆኑ የጥንቃቄ መልዕክት ማስተላለፍ ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።
''የሆቴል ባለሙያዎች ከሥራቸው አኳያ የበለጠ ተጋላጭ እንደመሆናቸው መንግስትም የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስና ኬሚካሎችን ለሆቴሎች በተለየ ሁኔታ ሊያቀርብ ይገባል'' ያሉት ደግሞ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ልዑልሰገድ መለሰ ናቸው።
በዚህም ላይ ማኅበሩ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጥምረት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
''ባለሙያዎች ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ እንግዶችን በጨዋነት ለማስተናገድ የሚያደርጉት ጥረት የሚበረታታ ነው'' ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ሥራቸው ከበርካታ ሰዎች ጋር የሚያገናኝ በመሆኑ በጤና ሚኒስቴር የሚሰጡ የጥንቃቄ መልዕክቶችን በአግባቡ በመተግበር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።
ከወራት በፊት መነሻውን ቻይና ባደረገው የኮሮና ቫይረስ በዓለም ላይ ከ235 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ ከ11 ሺህ በላይ የሚሆኑት ለህልፈት መዳረጋቸውን የዓለም የጤና ድርጅት ዛሬ ይፋ ያደረገው መረጃ ያመለክታል።