ቀጥታ፡

ኅብረቱ በሕዳሴ ግድብ ላይ የሚነሱ አለመግባባቶችን በመፍታት በኩል ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል - ምሁራን

መጋቢት 12/2012 (ኢዜአ) የአፍሪካ ኅብረት በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ የሚነሱ አለመግባባቶችን በመፍታት በኩል ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ምሁራን ገለጹ። 

ኢትዮጵያና ግብጽ በግድቡ ላይ ያላቸው ልዩነት በኀብረቱ በኩል እንዲፈታ ያደረጉት ጥረት ዝቅተኛ ነው ተብሏል። 

ምሁራኑ ኢትዮጵያና ግብጽ የጀመሩት የዲፕሎማሲ ዘመቻ በግድቡ ላይ ለተፈጠረው አለመግባባት መፍትሄ የሚሰጥ እንዳልሆነም ተናግረዋል።


አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአፍሪካ የሠላምና ደህንነት ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪዎች ዶክተር መረሳ ካሱ ና ዶክተር ዳዊት ዮሐንስ የአፍሪካ ኅብረት ኢትየጵያና ግብጽ በሕዳሴው ግድብ ግንባታ ላይ የጋራ መግባባት እንዲኖራቸው የማደራደሩን ስራ በግንባር ቀደምነት ሊሰራ ይገባል።


ኅብረቱ ከተቋቋመባቸው ዓላማዎች አንዱ የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካዊያን መፍትሄ እንዲያገኙ ማድረግ ቢሆንም በዚህ ረገድ ያደረገው ጥረት ደካማ መሆኑን ነው ያመለከቱት።

ይህም "የአፍሪካን ችግሮች በአፍሪካ መፍትሄዎች" የሚለውን መርህ የሚጥስ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ተመራማሪዎቹ ገለጻ በሕዳሴው ግድብ ላይ ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን የፈረሙት የመርህ ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆንና አገራቱ የዓባይን ውሃ በፍትሃዊነት እንዲጠቀሙ በማግባባት በኩል ኅብረቱ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል።


የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ ጀምሮ አገራቱ የየራሳቸውን የተሻሉ የድርድር ሀሳቦች በማምጣት ሲወያዩ ቢቆዩም በተለይ ግብጽ በግድቡ ውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ አልተስማማችም። 


ይህን አለመስማማት ለመፍታት ከአህጉራዊ ተቋማት ውጪ ሌሎች አገራት ጣልቃ መግባት እንደሌለባቸው የገለጹት ምሁራኑ ለዚህም የአፍሪካ ኅብረትን መጠቀም ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያና ግብጽ በግድቡ ላይ ያላቸው ልዩነት በኅብረቱ በኩል እንዲፈታ ያደረጉት ጥረት ዝቅተኛ መሆኑንም ምሁራኑ አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባለፈው ጥር በደቡብ አፍሪካ ጉብኝታቸው አዲሱ የኅብረቱ ሊቀመንበር የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ራማፎዛ በግድቡ ላይ ከግብጽ ጋር እንዲያደራድሩ መጠየቃቸውን በበጎ ጎን አንስተዋል።

በሁለቱም ወገን እንዲህ አይነት ፍላጎቶች ተጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸውና ሌሎች የኀብረቱ አባል አገራትም በዚህ ላይ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ገልጸዋል።


ኅብረቱ አባል አገራቱ በተናጠል ከሚያደርጉት ጥረት ባለፈ ገለልተኛ ሆኖ ኢትዮጵያና ግብጽን በማደራደር ወደ ስምምነት እንዲመጡ በማድረግ በኩል ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባልም ብለዋል።


ኅብረቱ በአህጉሪቷ ሠላምና መረጋጋት የማምጣት ሚናውን በአግባቡ ባልተወጣ ቁጥር ከቀጣናውና ከአህጉሪቷ ውጭ ያሉ ተዋንያን ጣልቃ በመግባት የሠላም ሂደቱን የማዛባት ዕድላቸው ከፍተኛ መሆኑንም ምሁራኑ አንስተዋል።


ይህ በአፍሪካ የተለያዩ አካባቢዎች ማጋጠሙን የሊቢያን ጉዳይ አብነት በመጥቀስ አስረድተዋል።


በሊቢያ በርካታ ተዋንያን በሠላም ድርድሩ ላይ እጃቸው በማረፉ የአገሪቷ የሠላም ጉዳይ መፍትሄ ሳያገኝ ዛሬ ድረስ ዘልቋል።


ኢትዮጵያ የዓባይ ውሃ በታችኞቹ የተፋሰሱ አገራት ላይ ጉልህ ጉዳት በማያስከትል መልኩ የመጠቀምና የመልማት መብቷን ማንም ሊፈቅድላትና ሊከለክላት እንደማይችልም ነው ምሁራኑ የገለጹት።


በመሆኑም በኢትዮጵያም ይሁን በግብጽ በኩል በቅርቡ በተለያዩ አገራት እየተካሄዱ ያሉ የዲፕሎማሲ ዘመቻዎች ከአገራቱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ከማጠናከር ባለፈ ስለ ግድቡ የጋራ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ መፍትሄ የማያመጣ መሆኑንም አመልክተዋል ።


ዶክተር መረሳ ካሱ  እንዳሉት ''በግብጽ በኩል ይጠቅመኛል የምትለውን የዲፕሎማሲ ስራ እየሰራች ከሆነ ኢትዮጵያም ይጠቅመኛል የምትለውን የዲፕሎማሲ ሥራ መስራት ክፋት የለውም።"

''ሁለቱንም ሊጠቅም የሚችል መፍትሄ ከማምጣት ይልቅ አንዱ የተሻለ አሸናፊ ሆኖ የሚወጣበት አማራጮችን ነው ሊፈጥር የሚችለው። "የሚለው ደግሞ ዶክተር ዳዊት ዮሐንስ ፡፡


በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ሂደት ኢትዮጵያና ግብጽ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ አልቻሉም።


በዚህ ምክንያት ግብጽ በተለይ የዓረብ አገራትን ድጋፍ ለማግኘት የተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻዎችን ማካሄድ እንደጀመረች ነው ምሁራኑ የገለጹት።


የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሽኩሪ በቅርቡ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ኩዌት፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች፣ ኳታርና ኦማን በማቅናት ግብጽ በዓባይ ውሃ ላይ ያላትን ተጠቃሚነትና ስለ ሕዳሴው ግድብ ማብራሪያ መስጠታቸውን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።


ኢትዮጵያም በፕሬዚዳንቷና በቀድሞ ፕሬዚዳንቷ የተመራ የልዑካን ቡድን ወደ አፍሪካና አውሮፓ አገራት በመላክ ስለ ግድቡ ያላትን አቋም አብራርታለች።


ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በኬንያና በኡጋንዳ ተገኝተው ከአገራቱ መሪዎች ጋር በግድቡ ውሃ አሞላል ላይ ስለተፈጠረው አለመግባባት አስረድተዋል።


የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመም ወደ አሜሪካና የተለያዩ የአውሮፓ አገራት የልዑካን ቡድን በመምራት ስለ ግድቡ ግንባታ ያለውን የተዛባ አመለካከት ለማጥራት ጥረት ያደርጋሉ ተብሏል።
ይሁንና የአገራቱ ችግር የሚፈታው በመካከላቸው በሚደረገው ውይይትና ድርድር ከዚያም ሲያልፍ አህጉራዊ ተቋም በሆነው የአፍሪካ ኀብረት ብቻ መሆኑን ምሁራኑ ያምናሉ።
የግድቡ መገንባት ከግብጽና ከሱዳን ባለፈ እንደ ጅቡቲ ከተፋሰሱ ውጪ ያሉ አገራትን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ በማድረግ በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም