በምስራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት ወረዳ በመስኖ የለማ የቆላ ስንዴ ማሳ ተጎበኘ

184

መጋቢት 12/2012 ኢዜአ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በምስራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት ወረዳ በመስኖ የለማ የቆላ ስንዴ ማሳን ጎበኙ።

በቦሰት ወረዳ ሲሳ በቴ ቀበሌ በተደረገው ጉብኝት ከአቶ ሽመልስ አብዲሳ በተጨማሪ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ እና በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የክልሉ የግብርናና ገጠር ዘርፍ አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴም ተሳትፈዋል።

በአካባቢው እየለማ የሚገኘው ስንዴ አገሪቱ ከውጭ የምታስገባውን የስንዴ ምርት ለማስቀረጥ ይረዳል ተብሏል።

በክልሉ ስንዴን በቆላማ አካባቢ የማልማት ስራ በአራት ዞኖች እየተከናወነ እንደሚገኝና እነዚህም ምስራቅ ሸዋ፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ ምዕራብ ሸዋ እና አርሲ ዞኖች መሆናቸው ተገልጿል።

ዛሬ በክልሉ ፕሬዝዳንት የተጎበኘው ስንዴ  ሰበል ሶስት ሺህ 300 ሄክታር ስፋት ያለው ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ የለማ መሆኑም ታውቋል።

በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ "ስንዴን በቆላማ አካባቢ የማምረት ተግባርን በክልሉ በሁሉም ዞኖች ለማስፋት እየተሰራ ነው" ብለዋል።

ተሞክሮው በአገር ደረጃ ተግባራዊ እንዲሆንም ከተለያዩ ክልሎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ዛሬ በምስራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት ወረዳ ሲሳ በቴ ቀበሌ የተጎበኘውና በአካባቢው አርሶአደሮች መሬት ላይ ተግባራዊ የተደረገው የቆላማ አካባቢ የስንዴ ምርት በአርሶአደሮች ጉልበትና በመንግስት ወጪና ድጋፍ የተከናወነ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም