በኦሮሚያ አለአግባብ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 1 ሺህ 085 የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ ሲወሰድ በ13 ነጋዴዎች ላይ ክስ ተመሠረተ - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ አለአግባብ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 1 ሺህ 085 የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ ሲወሰድ በ13 ነጋዴዎች ላይ ክስ ተመሠረተ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 12/2012(ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል የአቅርቦት ችግር ሳይኖር የኮሮና ቫይረስን ሰበብ በማድረግ አለአግባብ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 1 ሺህ 085 የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ ሲወሰድ በ13 ነጋዴዎች ላይ ክስ መመስረቱ ተገለጸ።
የኦሮሚያ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ገቢሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ የቫይረሱን ስርጭትን ለመከላከል የተለያዩ ኮሚቴዎች ተዋቅረው ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡
የተቋቋሙት ኮሚቴዎች የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችንና ቫይረሱን ሰበብ በማድረግ የሚፈጠሩ ሕገ ወጥነትን መከላከል ላይ እንደሚሠሩም ሃላፊው አስረድተዋል፡፡
የክልሉ መንግስት የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ የሚቀጠል መሆኑን የገለጹት አቶ ግዛቸው፣ ህብረተሰቡ መንግሥት ለሚወስደው የማስተካከያ እርምጃ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ክስ በተመሠረተባቸው 13ቱ ነጋዴዎች ላይ እንደጥፋታቸው መጠን አስተማሪ የሆነ ቅጣት እንደሚወሰንም አቶ ግዛቸው አመልክተዋል።
በኢትዮጵያ ዘጠኝ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ተጠቅተው በለይቶ ማቆያ የህክምና መስጫ ማእከል ውስጥ እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን፤ በለይቶ ማቆያ ህክምና እየተሰጣቸው ከሚገኙት ዘጠኝ ግለሰቦች ውስጥ አራቱ የበሽታው ምልክት መታየት ማቆሙን ሌሎች አራት ሰዎችም ደግሞ በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ መገለጹ ይታወሳል።
ትናት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ በሰጡት መግለጫ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ30 የበረራ መዳረሻዎች የሚያደርገውን ጉዞ እንዲያቋርጥ መወሰኑን መናገራቸው ይታወሳል።
ከተለያዩ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ሰዎችም በራሳቸው ወጪ በለይቶ ማቆያ ውስጥ ለ14 ቀናት እንዲቆዩ እንደሚደረግም መመሪያ ተላልፏል።