የኮሮና ቫይረስ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳው መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የኮሮና ቫይረስ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳው መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ
አዲስ አበባ ፣መጋቢት 11/2012 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የኮሮና ቫይረስ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳው መሆኑን አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እና ስርጭቱን ለመግታት ከተቋቋመው የሚኒስትሮች ኮሚቴ ጋር ዛሬ ተወያይተው ውሳኔ መተላለፉን ገልጸዋል።
በኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ እስካሁን 9 ሰዎች መያዛቸውን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ 4 ሰዎች በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ፤ 4 ሌሎች ሰዎች ደግሞ በመልካም ጤንነት ላይ መሆናቸውንና አንድ አዛውንት እናት ግን በከባድ ህመም ውስጥ ናቸው ብለዋል።
በሽታው በዓለም ላይ እያስከተለ ያለው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ በኢትዮጵያም በአግባቡ ካልተመራ ለከፋ ጉዳት የሚያጋልጥ መሆኑን አንስተዋል።
በዚህም መንግስት ባለፈው ከወሰናቸው ውስኔዎች ውጪ አዳዲስ ውሳኔዎችን የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እና ስርጭቱን ለመግታት የተቋቋመው የሚኒስትሮች ኮሚቴ መወሰኑን አስታውቀዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ 30 ሃገራት የሚያደርገውን በረራ እንዲያቋርጥ ተወስኗል ብለዋል።
ከየትኛውም አገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ መንገደኞች ለ14 ቀናት በልዩ ማቆያ (ኳራንቲን) የመቆየት ግዴታ እንደተጣለባቸው አንስተዋል።
ከእምነት ተቋማት ጋር በተያያዘ ከሀይማኖት አባቶች ጋር ንግግር መደረጉን እና የአምልኳቸው ሁኔታ ለቫይረሱ ስርጭት ምቹ ሊሆኑ ስለሚችል የራሳቸውን ውሳኔ እንዲያሳልፉም ከስምምነት ላይ መደረሱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
በማረሚያ ቤቶች ጋር በተያያዘ ቫይረሱ ከገባ ለቁጥጥር አስቸጋሪ ሁኔታ የሚፈጠር በመሆኑ ህጻናት ልጆችን የያዙ እናቶች እና የአመክሮ ጊዜያቸው የደረሰና ቀለል ያለ ክስ ያለባቸው ታራሚዎች እንዲለቀቁ መወሰኑን ተናግረዋል።
አዳዲስ እስረኞች ከበሽታው ነፃ መሆናቸው ሳይረጋገጥ ከሌሎች ታራሚዎች ጋር እንደማይቀላቀሉ እና በማረሚያ ቤቶች ሰዎች አንድ ላይ እንዳይሰባሰቡ ቦታ የማስፋት ስራ እንደተሰራም አንስተዋል።
በተጨማሪም የምሽት መዝናኛ ቤቶች ከዛሬ ጀምሮ አገልግሎት እንዳይሰጡና ሙሉ ለሙሉ እንዲዘጉ መወሰኑንም ተናግረዋል።
በውጭ አገራት ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን መገለል እና ጥቃት በማውገዝ ፤ ቫይረሱ ቀለም፣ ጾታ እና ሃይማኖት የማይለይ በመሆኑ ማንኛውም ሰው ከዚህ አይነቱ ድርጊት እንዲቆጠብም እና በፍፁም ኢትዮጵያዊ ጨዋነት እንዲያስተናግድ አሳስበዋል።
በአዲስ አበባ ወጣቶች በበጎ ፍቃድ እየሰጡት ያለውን አገልግሎት በማድነቅም በቀጣይ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ምርጫን በተመለከተ ምርጫ ቦርድ የበሽታውን ስርጭት አይቶ የራሱን ግምገማ እንደሚያቀርብ እና በዛ ጥናት እንደሚታይ እና ችግሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚታለፍ ከሆነ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ቢካሄድ ጥሩ መሆኑን አንስተዋል።
ህገወጥ ነጋዴዎችን በተመለከተ የንግዱ ማህበረሰብ ዓለም አቀፍ ፈተና የሆነውን በሽታ ለመከላከል ያለውን የሚያካፍልበት እንጂ ከሌላቸው ሰዎች የሚዘርፍበት አለመሆኑንም አንስተዋል።
በሽታው በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ እያሳደረ ያለውን ጫና በሚመለከት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበሽታው ሳቢያ ከ190 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ለኪሳራ መዳረጉን ተናግረዋል።
የህክምና ባለሙያዎች ልክ እንደ አገራዊ ግዳጅ ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ እና እስካሁን ላበረከቱት አስተዋፆ አመስግነው የጀመሩትን ጥረት እንዲያጠናክሩ ተናግረዋል።
በመንግስት ሆስፒታሎች አስላጊው ዝግጅት ተደርጎ እየሰሩ መሆኑን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የግል ሆስፒታሎችም አቅም በፈቀደ መጠን ዝግጅት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ከመጠጥ ውሃ ጋር በተያያዘ እጥረት ባለበት አካባቢ ተጨማሪ ቦቴዎች ለማቅረብ መንግስት ጥረት እንደሚያደርግ እና በከተሞች እየተሰሩ ያሉ ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ጃክ ማ እና ቢል ኤንድ ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ለአፍሪካ ሊሰጥ ያቀዳቸው 20 ሺህ መመርመሪያ መሳሪያዎች እና 1 ሚሊዮን የሚጠጋ የፊት መሸፈኛ ከነገ በስቲያ እሁድ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በውጪ ንግድ የአበባ እና የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች ተቀባይ አገራት ምርቶቹን መቀበል በማቆማቸው ዘርፉ መቀዛቀዙን በማንሳት ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ እቃዎች ላይም እንዲሁ ጫና ማሳደሩን አስረድተዋል።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የቢልጌት ፋውንዴሽንን ጨምሮ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን አንስተው በዚህም ከ80 ሚሊዮን ዶላር በላይ የመንግስትንም ጨምሮ የዜጎች ህይወት እንዳይጠፋ መመደቡን ተናግረዋል።
መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ራሱን ከቫይረሱ በመከላከል ሌሎችንም እንዲከላከል ጥሪ አቅርበው አሁን የገጠመውን ፈተና በጋራ ሆኖ መከላከል እንደሚገባና ሚዲያዎችም በዚህ ረገድ ሚናቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
በመጨረሻም አሁን ላይ ትንንሽ ጉዳዮች ላይ ሳናተኩር የኮሮና ቫይረስን በመከላከልና የጂኦ ፖለቲክሱን ሁኔታ በትኩረት በመከታተል ከአገራት ጋር በትብብር መስራት ይገባል ብለዋል።