ቀጥታ፡

ዶክተር ካትሪን ሃምሊን የራሳቸውን ህይወት ትተው ለሌሎች ኖረው ያለፉ ታላቅ ሰው - አስተያየት ሰጭዎች

አዲስ አበባ ፣መጋቢት 11/2012 (ኢዜአ) ዶክተር ካትሪን ሃምሊን፤ ለሰው ልጆች በጽናት መቆምን፣ ፍቅርንና ለሌሎች መኖርን ያስተማሩ ታላቅ ሰው መሆናቸውን አስተያየት ሰጭዎች ተናገሩ።


አዲስ አበባ ፣መጋቢት 11/2012 (ኢዜአ) ዶክተር ካትሪን ሃምሊን፤ ለሰው ልጆች በጽናት መቆምን፣ ፍቅርንና ለሌሎች መኖርን ያስተማሩ ታላቅ ሰው መሆናቸውን አስተያየት ሰጭዎች ተናገሩ።


ዶክተር ካትሪን ሃምሊን በኢትዮጵያ የፊስቱላ ሆስፒታልን በማቋቋም ከ60 ዓመታት በላይ የፌስቱላ ሕክምና እንዲሰጥ ሲያደርጉ ቆይተዋል።


በዚህም የፊስቱላ ችግር ገጥሟቸው ለከፍተኛ ችግር የተጋለጡና በህብረተሰቡ ዘንድ መገለል የደረሰባቸውን ኢትዮጵያዊያን ሴቶችን ህይወት መታደግ የቻሉ እንስት ናቸው።


ዶክተር ሃምሊን ፊስቱላ የሚያስከትለውን ዘርፈ ብዙ ችግር ተገንዝበውና በኢትዮጵያ ያለውን እጥረት በመረዳት ከባለቤታቸው ዶክተር ሬጂናልድ ሃምሊን ጋር የህክምና አገልግሎት መስጫ ማዕከል በመቋቋም ከ60 ሺህ በላይ ሴቶችን ህይወት ታድገዋል።


ዶክተር ካትሪን ሃምሊን በሙያቸው ለፊስቱላ ችግር የተዳረጉና እርዳታ ለሚሹ ኢትዮጵያዊያን ሴቶች የሕክምና ፣ የገንዘብና የቁሳቁስ እርዳታና ድጋፍ በማድረግ መልካም ሥራ ሰርተው ያለፉ ሴት ናቸው።


በዚህም የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያዊያን በሃምሊን ሆስፒታል ቅጥር ግቢ ውስጥ በመገኘት ሀዘናቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።


ዶክተር ሀምሊን ለተጎዱ ዜጎች በጽናት መቆምንና የሰብዓዊነትን ጥግ በተግባር ያሳዩ ታላቅ ሴት መሆናቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።


የራሳቸውን ህይወት ትተው ለሌሎች የኖሩ እንደመሆናቸው ኢትዮጵያዊያን ዜጎችም ከእሳቸው ብዙ መልካም ነገሮችን መማር እንደሚችሉ ገልጸዋል።


ወይዘሮ ማሚት ጋሼ ዶክተር ሀምሊን ከህመማቸው እንዲድኑ እገዛ እንዳረጉላቸውና ከእሳቸው በርካታ ነገሮችን መማራቸውን ተናግረዋል።


ሌሎች የጤና ባለሙያዎችም አርአያቸውን ተከትለው ለህመምተኞች ፍቅርን እያሳዩ በመደገፍ ከበሽታቸው እንዲድኑ በማድረግ ቢሰሩ መልካም ነው ብለዋል።


ወይዘሮ ኬለሽ ገረመው በበኩላቸው ዶክተር ሀምሊንና ባለቤታቸውን በህመማቸው ወቅት ያገኟቸው እናትና አባታቸው መሆናቸውን ነው የገለጹት።


"እኛም ህይወታችን እስካለ ድረስ እሳቸው ያደረጉትን የሚሰሩት የነበሩትን ነገር ለመርዳት ነው የምንፈልገው" ብለዋል።


ሲስተር ጤና አዳም አቀለ ከእሳቸው ጀምሮ ሌሎች ነርሶችም በሆስፒታሉ ህክምና ካገኙ በኋላ ስልጠና ወስደው ሌሎች ሴቶችን ሲረዱ መቆየታቸውን ነው የተናገሩት።


ዶክተር ሀምሊንን ሌጋሲ ለማስቀጠል "እኛ ልጆቿ ትልቅ ኃላፊነት ነው ጥላብን ያለፍነው።" ሲሉም ተናግረዋል።
የሃምሊን ሆስፒታል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተስፋዬ ማሞ በበኩላቸው "ዶክተር ካትሪን በኢትዮጵያ የሕክምና አገልግሎት ውስጥ አርአያነታቸው ከፍተኛ ነው" ይላሉ።


ለፊስቱላ ችግር የተዳረጉ ሴቶች ከማህበረሰቡና ከቤተሰቦቻቸው ተገልለው በተቀመጡበት ወቅት ህይወታቸው እንዲለወጥና የኢኮኖሚ አቅማቸው እንዲዳብር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውንም ተናግረዋል።


እንደ አቶ ተስፋዬ ገለጻ የድርጅቱ አገልግሎት ወደ ፊት እንዲቀጥል ፊስቱላን በመከላከል በኩል በገጠር ጤና ጣቢያዎች ስትራቴጂ ተነድፎ እየተሰራ ይገኛል።


በመሆኑም ዶክተር ሃምሊን ለዜጎች በጽናት የመቆምና ህዝቦችን የማዳን ትልቅ ኃላፊነትን ጥለው ያለፉ በመሆኑ ራዕያቸውን ለማሳካት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።


ዶክተር ካትሪን ሃምሊን በኢትዮጵያ ላከናወኗቸው መልካም ተግባራት በመንግስት የክብር ዜግነት እንዲሁም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ የክብር ዶክትሬት የተሰጣቸው መሆኑ የሚታወስ ነው።


የሃምሊን ፊስቱላ ሆስፒታል ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በመቀሌ፣ በባህርዳር፣ በይርጋለም፣ በሐረርና መቱ ከተሞች ቅርንጫፍ በመክፈት እየሰራም ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም