ቀጥታ፡

ለህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ የህዝቡ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ

ባህርዳር ፣መጋቢት 11/2012 (ኢዜአ) የህዳሴ ግድብን ወደ መጨረሻው የድል ምዕራፍ ለማሸጋገር የህብረተሰቡ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በአማራ ክልል የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የግድቡ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበት 9ኛ ዓመት በክልል ደረጃ በተለያዩ ዝግጅቶች ለማክበር እየተሰራ መሆኑ ተመልክቷል።

የማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ላቀ ጥላዬ ለኢዜአ እንደገለጹት የህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያ ህዝብ ሙሉ ተሳትፎ እየተገነባ የሚገኝ ሃገራዊ ፕሮጀክት ነው።

በዚህም የአማራ ክልል ህዝብ እስከ አሁን ከአንድ ነጥብ አንድ ቢሊየን ብር በላይ በቦንድ ግዥ፣ በስጦታና በተለያዩ የገቢ ማስገኛዎች በመሳተፍ ግድቡ አሁን ካለበት እንዲደርስ አስተዋጽኦ ማድረጉን አውስተዋል።

በመጪው መጋቢት 24/2012 ዓ.ም የሚከበረውን የ9ኛ ዓመት በዓል ምክንያት በማድረግ በሚካሄደው የቦንድ ግዥ ሳምንትም ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ እንቅስቃሴ እየተካሄደ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ከዝቅተኛ እሰከ ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኘውን ህዝብ የሚሳተፍበት የ8100 መልዕክት መላኪያ ፕሮግራም ይፋ መደረጉን ጠቁመው፤ ህብረተሰቡ ቀደም ሲል ያደርግ ከነበረውን የገንዘብ ድጋፍ በተሻለ ንቃት እንዲሳተፍ ጠይቀዋል።

በየደረጃው ስለግደቡ መረጃ የሚሰጡ የጥናት ስራዎችን በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን በፓናል ውይይቶች በማቅረብ ሀገራዊ፣ ቀጠናዊና አህጉራዊ ፋይዳውን ለህዝብ የማስረጽ ስራም እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

የአባይ ወንዝ ተፋሰስን ለመጠበቅ ህዝቡ በተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ እንዲሳተፍ በማድረግ ከ24 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት የጉልበት አስተዋጽኦ እንዲያበረክት መደረጉንም ተናግረዋል።

ይህም ወደ ግድቡ የሚገባውን ደለል በመቀነስ ለረጅም ዘመን አገልግሎት እንዲሰጥ የሚየስችል መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህ ዓመትም የአፈርና ውሃ እቀባ ስራው በልዩ ትኩረት ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።

ግድቡን ወደ መጨረሻው የድል ምዕራፍ በማሸጋገር ከውጭ ጣልቃ ገብነት ለመላቀቅ ህብረተሰቡ በገንዘቡ፣ በጉልበቱና በእውቀቱ የጀመረውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት አቶ ላቀ መልዕክት አስተላልፈዋል። 

የመንግስት ሰራተኛ የሆኑት አቶ አዲሱ ዘመነ በበኩላቸው ሰሞኑን መስሪያ ቤታቸው ባዘጋጀው የጉብኝት ፕሮግራም መሳተፋቸው ስለ ህዳሴ ግድብ ሲሰሙት ከነበረው በላይ ታላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት መሆኑን ማረጋገጥ መቻላቸውን ጠቅሰዋል።

አሁን ላይ ሁለቱን የሃይል ማመንጫ ተርባይኖችን ወደ ስራ ለማስገባት የሚያስችል የመገጣጠም ስራ እየተፋጠነ እንደሚገኝ በአይናቸው ማየታቸው ለግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ ጉጉት እንዳሳደረባቸው ገልፀዋል።

የባህርዳር ከተማ ነዋሪው አቶ ግርማ ታደገ በበኩላቸው እንደተናገሩት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ማጠናቀቅ የመኖርና ያለመኖር የህልውና ጥያቄን የመመለስ ጉዳይ ነው።

በአሁኑ ወቅት የግብጽ መንግስት የግድቡን ግንባታ ለማስቆምና ውሃ በመያዝ የሚፈለገውን ጥቅም እንዳይሰጥ የሚያደርገውን ጥረት ለማክሸፍ ከህብረተሰቡ ጋር እሳቸውም የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል።

በ2003 ዓ.ም የተጀመረውና ግንባታው ሲጠናቀቅ ስድስት ሺህ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል የሚያመነጨው ታለቁ የኢትዮጵ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አሁን ላይ ከ71 በመቶ በላይ መጠናቀቁ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም