ቀጥታ፡

በሀዋሳ ከተማ ህብረተሰቡን ከኮሮና ቫይረስ ለመጠበቅ እየተሰራ ነው

ሀዋሳመጋቢት 11/2012 (ኢዜአ) በሀዋሳ ከተማ ህብረተሰቡን ከኮሮና ቫይረስ ለመጠበቅ የቅድመ ጥንቃቄ ስራ እየተካሄደ መሆኑን የከተማው አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ገለጹ።

ምክትል ከንቲባው አቶ ጥራቱ በየነ እንዳሉት በሽታውን ለመከላከል ለህብረተሰቡን ግንዛቤ የሚያስጨብጥና  ሌሎች የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎችን የሚመራ ግብረ ኃይል ተቋቁሟል።

የመንግስት አገልግሎት መስጫ ተቋማት፣ ሆስፒታሎች፣ ሆቴሎች፣ ማረሚያ ቤቶችና ኢንዱስትሪ ፓርክን ጨምሮ  ተገልጋዮችና ሠራተኞች ሲገቡም ሆነ ሲወጡ እንዲታጠቡ ውሃና ሌሎች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች እንዲሟሉ ተደርጓል።

በዚህም ቫይረሱን በመከላከል ህብረተሰቡን ከበሽታው ለመጠበቅ  በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ምክትል ከንቲባው  ገልጸዋል።

በሽታው ቢከሰት እንኳን ሳይስፋፋና ጉዳት ሳያደርስ ለመቆጣጠር አስፈላጊ ቁሳቁሶች የተሟላለት የለይቶ ማቆያ ከከተማ ወጣ ባለ ስፍራ ከጤና ባለሙያዎች ጋር መመቻቸቱን አስታውቀዋል፡፡

የከተማዋ አመራሮች ወደ አስተዳደሩ ለተለያዩ ጉዳዮች የሚመጡ ተገልጋዮች ማድረግ ስለሚገባቸው ጥንቃቄ በተግባር የተደገፈ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እየሰጡ ነው።  

በአንድ ላይ የሚያስተናግዱ የአምልኮ ስፍራዎች ህብረተሰቡ ከእጅ ንክኪ በመቆጠብ ጥንቃቄ እንዲያደርግም አቶ ጥራቱ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ታርኳ ዮሐንስ በሰጡት አስተያየት ከመንግስትና ከጤና ባለሙያዎች በደረሳቸው የጥንቃቄ መልዕክት መሰረት በሽታውን ለመከላከል የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ነዋሪው  እራሱን በመጠበቅ  በሽታውን  ለመከላከል ጥረት ማድረግ እንዳለበትም አመልክተዋል።

በከተማዋ  የተለያዩ ተቋማት ተገልጋዩ ሲገባና ሲወጣ የንጽህና መጠበቂያ ውሃ፣ ሳሙና መሰል ቁሳቁሶች ማዘጋጀታቸው  የሚያስመሰግን መሆኑን የተናገሩት ደግሞ አቶ ዝናቡ አብርሃም የተባሉ  ነዋሪ ናቸው።

ቫይረሱን ለመከላከል ንጽህናቸውን በመጠበቅና ከንክኪ በመራቅ  የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ መሆኑንም ገልጸዋል።

በደቡብ ክልል ሁሉም ዞኖች በሽታውን የመከላከሉን ስራ ውጤታማ ለማድረግና ከተከሰተም ሳይስፋፋ ለመቆጣጠር የለይቶ ማቆያ ስፍራዎች እንዲደራጁ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ ቀደም ብሎ ገልጿል።

መረጃዎችና ምክሮችን ከመንግስትና ከጤና ባለሙያ ብቻ መውሰድና ተግባራዊ በማድረግ ህብረተሰቡ የጋራ ሃላፊነት ወስዶ እንዲቀሳቀስም መልዕክት ተላልፏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም