በመዳ ወላቡና ጅማ ዩኒቨርሲቲዎች ኮሮና የመከላከል ስራ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በመዳ ወላቡና ጅማ ዩኒቨርሲቲዎች ኮሮና የመከላከል ስራ እየተከናወነ ነው
ጎባ ፤ ጅማ መጋቢት 11/2012 ( ኢዜአ ) በመዳ ወላቡና ጅማ ዩኒቨርሲቲዎች የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚያስችል ስራ እየተከናወነ መሆኑን ዩኒቨርሲቲዎቹ ገለፁ ።
በመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ የተቋቋመው ግብረ ኃይል በሮቤ፣ጎባና ሻሻመኔ ካማፓሶች የተቀናጀ የመከላከል ስራ እያከናወነ መሆኑን ተገልጿል ።
የዩኒቨርሲቲው የውጭና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ዶክተር ዘለቀ ረጋሳ ለኢዜአ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል በሮቤ፣ ጎባና ሻሻመኔ ካምፓሶች የተለያዩ ንኡስ ኮሚቴዎች ተቋቁመው ወደ ስራ ገብተዋል ።
ተማሪዎች በመኝታ ክፍላቸው ውስጥ ተወስነው እንዲማሩ በተላለፈው መመሪያ መሰረት የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችን በሶፍት ኮፒና በጽሁፍ ተደራሽ በማድረግ ትምህርታቸውን እንዲያጠኑ መደረጉን አስረድተዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከራሱ ተማሪዎችና ሰራተኞች በተጨማሪ በከተማዋ የሚገኙ የማህበረሰብ አካላት ስለ በሽታው አውቀው ራሳቸውን እንዲጠብቁ ለማስቻል የግንዛቤ ማስጨበጫ በራሪ ወረቀቶችን በማሳተም ተደራሽ እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ከተማሪዎች መካከል ኤፍሬም ጥላሁን እንደገለጸው "የተቋቋመው ግብረ ሀይል በሳሙናና አልኮል እጃችንን በመታጠብ በሽታውን በምንችለው አቅም እንድንከላከል እገዛ እያደረገልን ይገኛል" ብሏል፡፡
የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ከ23 ሺህ 900 በላይ ተማሪዎችን በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር በተለያዩ ፕሮግራሞች በማስተማር ላይ እንደሚገኝ ከዩኒቨርሲቲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
በተመሳሳይ የጅማ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ቫይረሱን ለመከላከል የሚያስችል ጥንቃቄ እያደረጉ መሆኑን ገለፀዋል።
ኢዜአ ካነጋገራቸው ተማሪዎች መካከል የሁለተኛ አመት የኢኮኖሚክስ ተማሪ ተስፋዬ ገመቹ እንደገለጸው የመተላለፊያ መንገዶችን አስመልክቶ የሚተላለፉ መልዕክቶችን ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግሯል፡፡
ህዝብ በሚበዛበት አካባቢ ባለመገኘትና ንፅህና መጠበቅ በየዕለቱ የሚተገብራቸው ዋነኞቹ ተግባራት እንደሆኑ ገልጿል፡፡
በሚዲያና ከዩነቨርስቲው የሚተላለፉልንን የጥንቃቄ መልዕክቶችን ተግባራዊ ማድረግ ላይ ትኩረት መስጠቷን የተናገረችው ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያ አመት ተማሪ አብነት አሸናፊ ናት።
"ዩኒቨርስቲያችን በተለያዩ ቦታዎች የእጅ መታጠቢያ ውሃና ሳሙና ማዘጋጀቱ፤ የመመገቢያ ሰአት ማራዘሙና የሚሰጠን ምክርና ድጋፍ የሚያረጋጋ ነው" ብላለች፡፡
የጅማ ዩኒቨርስቲ ፕሬዘዳንት ዶክተር ጀማል አባፊጣ እንደገለጹት በዩኒቨርስቲው ሆነ በከተማ ውስጥ ቫይረሱ እንዳይከሰት ከተከሰተ ደግሞ ተገቢውን ህክምና ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል፡፡
ከተደረጉት ዝግጅቶች ውስጥም በአራት ንዑስ ኮሚቴ የተደረጀ 26 አባላት ያሉት ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል፡፡
እነዚህ አካላት የግንዛቤ ፈጠራ፣ የማረጋጋት ስራ፣ የተማሪዎችን የህብረት እንቅስቃሴ መገደብ፣ የክፍል ውስጥ ትምህርትና የላይብረሪ አገልግሎት ማቋረጥ፣ በአርባ ስፍራዎች የእጅ መታጠቢያ አማራጮች ማስቀመጥ ፣ የመመገቢያ ሰአት ማራዘምና በተራራቀ ሁኔታ እንዲቀመጡ ማድረግ የመሳሰሉ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ፡፡
ቫይረሱ ከተከሰተ ህክምና የሚሰጡ 12 ሃኪሞችን አሰልጥኖ ዝግጁ ማድረጉንም ከዩኒቨርሲቲው የተገኘው መረጃ ያመላክታል ።