የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ለኮሮና ቫይረስ መከላከያ 20 ሚሊዮን ብር መደበ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ለኮሮና ቫይረስ መከላከያ 20 ሚሊዮን ብር መደበ
አዲስ አበባ ፤መጋቢት 11/2012 የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚውል 20 ሚሊዮን ብር መመደቡን አስታወቀ።
የማህበሩ ዋና ፀሃፊ ዶክተር መሸሻ ሸዋረጋ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እየተከናወነ ያለውን ዝግጅት በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።
ማህበሩ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ከዓለም አቀፍ የቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ፌደረሽን እንዲሁም ከእህት ማህበራት ጋር በመሆን የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም 5 ሺህ የፊት መሸፈኛ ማስኮች፣ 6 ሺህ የሰርጅካል ጓንቶችን፣ 1 ሺ 500 የህክምና ጫማዎች፣ 1 ሺህ የፕላስቲክ የፊት መከላከያ እና 5 ሺህ የመለያ ገዋኖችን ለመግዛት መታቀዱንም ዶክተር መሸሻ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ከ500 በላይ አምቡላንሶች አስፈላጊው የህክምና ቁሳቁስ ተሟልቶላቸው ዝግጁ ሆነዋል ነው ያሉት።
ማህበሩ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል በፌዴራል እና በክልል ያሉት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶቹን በማስተባበር እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
የማህበሩ በጎ ፍቃደኞች ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን በአየር ማረፊያ፣ ከአጎራባች ሃገራት ወደ ኢትዮጵያ መግቢያ ኬላዎች ለሚገቡ ሰዎች የሙቀት ልየታ እየሰሩ መሆኑ ተገልጿል።
እንደ ዶክተር መሸሻ ገለፃ የማህበሩ አባላት የጤና ሚኒስቴር እና የክልል ጤና ቢሮዎች ባቋቋማቸው አብይና የቴክኒክ ኮምቴዎች ውስጥም በመሳተፍ ላይ ናቸው።
ማህበሩ ከ4000 በላይ ለሚሆኑ ከባለድርሻ አካላት ለተውጣጡ ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መስጠቱንም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ አሁን ላይ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 9 መድረሱ ይታወቃል።