እየተስፋፋ የመጣው የቴሌኮም ማጭበርበርና የፋይቨር ጥቃት ወንጀል በአገሪቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
እየተስፋፋ የመጣው የቴሌኮም ማጭበርበርና የፋይቨር ጥቃት ወንጀል በአገሪቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ነው
አዲስ አበባ ሰኔ 22/2010 ኢትዮጵያ ውስጥ ከቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ጋር በተያያዘ እየተስፋፋ የመጣው የማጭበርበርና የፋይቨር ጥቃት ወንጀል በአገሪቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ መሆኑ ተገልጿል። ወንጀሉ አገሪቱን በየዓመቱ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ኃብት እያሳጣት ነው ተብሏል። ከቴሌኮም አገልግሎት ጋር በተያያዘ የሚስተዋለውን የማጭበርበርና ህገ-ወጥ አሰራር መከላከል በሚቻልበት መንገድ ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ከባለድርሻ አካላት ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሄዷል። የኢትዮ-ቴሌኮም የኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት ዳይሬክተር አቶ አብዱራሂም አህመድ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት፤ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል እየተስፋፋ በመምጣቱ ከተቋሙ ባሻገር በአገር ደህንነት ላይ አደጋ ደቅኗል። የተቋሙ ሰራተኞችን ጨምሮ የሲም ካርድ ጅምላ አከፋፋዮች፣ በመኖሪያ ቤቶችና ሆቴሎች በወንጀል ተግባሩ ከሚሳተፉት ተዋናዮች መካከል መሆናቸውንም ገልፀዋል። ከአገር ውጭም አገልግሎት ሰጪ ኦፕሬተሮችና መልዕክት አስተላላፊ ድርጅቶች የሚሳተፉበት አደገኛ ድርጊት መሆኑን ተናግረዋል። በሚፈፀመው በዚህ የቴሌኮም ማጭርበር ወንጀል አገሪቱ በየዓመቱ በአማካይ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ እያጣች መሆኑንም የጠቆሙት አቶ አብዱራሂም ይህም አገራዊውን የፋይናንስ ደህንነት ለስጋት የሚጥል መሆኑንም ተናግረዋል። በአገሪቱ ያልተመዘገቡ ሲም ካርዶች አማካኝነት የ'ሲምቦክስ' ተጠቅመው የውጭ ጥሪዎችን ወደ ግል በማዞር መልዕክትን የማስተላለፍ ወንጀልን ለመከታተል አስቸጋሪ መሆኑነ የጠቀሱት አቶ አብዱራሂም ይህም የአገሪቱ ደህንነት ስጋት ላይ እንደሚጥል ገልፀዋል። በአዲስ አበባ ኢትዮ-ቴሌኮም መሰረተ ልማቶች ላይ እየተፈፀመ ያለው ስርቆት በአገልግሎት አሰጣጡና ደህንነት ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑንም አስታውቀዋል። በተለይ በዚህ ዓመት በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ በቴሌኮም የፋይቨር ቴክኖሎጂ ቁሳቁሶች ላይ የተፈፀመው ስርቆት ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ለአብነተ አንስተዋል። በግንዛቤ መስጫ መድረኩ የተገኙት የየካ ክፍለከተማ ነዋሪ በአገር ውስጥ ለቴሌኮም ማጭበርበር የሚውሉ መሳሪያዎች ለመቆጣጠርና የመሰረተ ልማቱን ከጉዳት ለመከላከል ከማህበረሰቡ ጋር በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል። ሌላው ተሳታፊ የአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ኑር መሐመድ በበኩላቸው በኢትዮ-ቴሌኮም መሰረተ ልማት ላይ የሚፈፀሙትን ወንጀሎች ለመከላከል ከማህበረሰቡና ከፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት ከመስራት አኳያ የሚታየው ድክመት ሊቀረፍ ይገባል ነው ያሉት። ቴሌኮምን፣ መብራት ኃይልን፣ የውሃና ፍሳሽን የመሳሰሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ተናበውና ተቀናጅተው አለመስራታቸው አገሪቱን ለበርካታ የኃብት ውድመት እየዳረጋት መሆኑን ተሳታፊዎች አንስተዋል። የኢትዮ-ቴሌኮም መሰረተ ልማት ቁሳቁሶች ሰርቆት ባሻገር መስሪያ ቤቱ ጥበቃ በማይደረግላቸው ክፍት ቦታዎች የሚያከማቻቸውን የተለያዩ ቁሳቁሶች በወቅቱ ሳያነሳቸው በመቅረቱ ለስርቆት እንደሚዳረጉም ተሳታፊዎቹ ገልፀዋል። በተለይ የቴሌኮም ማጭበርበሩ ከሀብት ማሳጣት በተጨማሪ የአገር ደህንነትን አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ ተገቢው ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አሳስበዋል። በውይይቱ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው እንዳሉት፤ በኢትዮ-ቴሌኮም መሰረተ ልማት ላይ የሚደርሰውን ጉዳትና የሚፈፀመውን የማጭበርበር ወንጀል ለመከላከል ከህዝብ ጋር መስራት ወሳኝ ነው። በተለይ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል የአገር ደህንነትም አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ አጥፊዎችን እየተከታተሉ ለህግ ማቅረብ ያስፈልጋል ነው ያሉት። በኢትዮ ቴሌኮም፣ መብራት ኃይል፣ የውሃና ፈሳሽ አገልገሎት ተቋማት አማካኝነት የሚካሄዱ የመሰረተ ልማት ዝርጋት ተግባራት አለመቀናጀት የሚፈጥረውን ችግር ለመከላከል የሚያስችል ስልት እየተቀየሰ መሆኑን ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል። የኢትዮ ቴሌኮም የኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት ዳይሬክተር አቶ አብዱረህማን አህመድ በበኩላቸው ችግሩን ለመፍታት ግንዛቤ ከመፍጠር ባሻገር የሲምካርድ ሽያጭ፣ የቴሌኮም ቁሳቁሶች እና የቴክኖሎጂ ቁጥጥር እንዲሁም ወንጀለኞችን ወደ ህግ ለማቅረብ የሚያስችሉ ሰፋፊ ተግባራት እንደሚከናወኑ ገልፀዋል። በመድረኩ የተነሱ ሃሳቦችና አስተያየቶችም ኢትዮ ቴሌኮም ችግሩን ለመፍታት ለሚወስዳቸው እርምጃዎች በግብአትነት እንደሚጠቀምበትም ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከ21 ሺህ ኪሎሜትር በላይ የፋይቨር ኦፕቲክ ገመድ ተዘርግቷል። የኢትዮ-ቴሌኮም በመላው ኢትዮጵያ 64 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሞባይል ተጠቃሚዎችን ጨምሮ በድምሩ ከ66 ሚሊዮን በላይ የስልክ ደንበኞች አሉት። አገሪቱ ባለፉት 12 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ብቻ ሶስት ቢሊዮን ዶላር ለቴሌኮም መሰረተ ልማት ግንባታ መዋዕለ ንዋይ ፈሷል።