ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ ጎፋ ገብርኤል አካባቢ በደረሰ የእሳት አደጋ ሁለት የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ጉዳት ደርሶባቸዋል

አዲስ አበባ ፣መጋቢት 11/2012 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ፣ በአንድ ጋራዥ ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ ሁለት ሰዎች ሲጎዱ ከ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ወደመ።

በአዲስ አበባ፣ ወረዳ 6 በተለምዶ ጎፋ ገብርኤል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በአንድ ጋራዥ ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ ሁለት የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ጉዳት ሲደርስባቸው ከ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረትም ወድሟል።
የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ቡድን መሪ አቶ ጉልላት ጌታነህ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የእሳት አደጋው የደረሰው ትናንት ምሽት 2 ሰዓት ከ50 አካባቢ ነው።

የእሳት አደጋው በአንድ ጋራዥ ላይ የደረሰ ሲሆን እሳቱን ለማጥፋት ከተሰማሩት 71 የእሳት አደጋ ሰራተኞች መካከል ሁለቱ ቀላል ጉዳት አጋጥሟቸዋል ተብሏል።

ከዚህ በተጨማሪ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ሲወድም ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ከቃጠሎው ማትረፍ መቻሉን አቶ ጉልላት ገልጸዋል።

እሳቱን ለመቆጣጠር አምስት ሳአታትን የፈጀ የማጥፋት ስራ የተከናወነ ሲሆን 250 ሺህ ሊትር ውሃ ጥቅም ላይ ውሏል።

እንደ አቶ ጉልላት ገለፃ፤ በእለቱ አምቡላንስን ጨምሮ 12 የእሳት አደጋ ተሽከርካሪዎች ውሃ በመርጨትና በማመላለስ ተሳትፈዋል።

የእሳት አደጋውን በመቆጣጠር ሂደት የፌዴራል እና አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች ከፍተኛ ርብርብ ማድረጋቸውም ታውቋል።

በጋራዡ ላይ ከደረሰው ቃጠሎ በተጨማሪ ወደ አካባቢው ነዋሪዎች እንዳይዛመት መደረጉን የተናገሩት አቶ ጉልላት፤ የአደጋው መንስኤ በመጣራት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም