ቀጥታ፡

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የኮሮና ቫይረስ መዛመትን ለመግታት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 10/2012 (ኢዜአ) የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ስርጭትን ለመግታት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን በአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የበሽታዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል (ሲዲሲ) አስታወቀ።

ማዕከሉ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ኮቪድ 19 በተሰኘው ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ሳቢያ እስካሁን በአፍሪካ የ16 ሰዎችን ህይወት ሲቀጥፍ፤ 640 ሰዎች ደግሞ በወረርሽኙ መያዛቸውን ይፋ አድርጓል።

የአፍሪካ ሲዲሲ ዳይሬክተር ዶክተር ጆን ኒኬንጋሶንግ እንዳሉት፤ በዓለም ላይ ከ200 ሺህ በላይ ሰዎች በኮቪድ-19 ሲጠቁ፣ ከነዚህም መካከል 640 የሚሆኑት በ34 የአፍሪካ አገሮች ይገኛሉ።

ከአገሮቹ መካከል ግብጽ 210፣ ደቡብ አፍሪካ 116፣ አልጀሪያ 72፣ ሞሮኮ 54፣ ሴኔጋል 36 ተጠቂዎችን ይዘዋል።

የሟቾችን መረጃ በተመለከተም በአልጀሪያ፣ ግብጽ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ናይጄሪያ፣ ሴኔጋልና ካሜሩን በአጠቃላይ 16 ሰዎች ለሕልፈተ ሕይወት መዳረጋቸውን ይፋ አድርገዋል።

በሌላ በኩል 41 ህሙማን ከበሽታው ማገገማቸውን ተናግረዋል።

ይህን ተከተሎ የአፍሪካ ሕብረት በአባል አገሮቹ ስለ በሽታው ወቅታዊ መረጃ ልውውጥና በየአገሩ ለሚገኙ የጸረ ኮሮናቫይረስ ግብረ ሃይላት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አፍሪካ ሲዲሲ ከ6 ሺህ በላይ ሰዎችን ለመመርመር የሚያስችሉ መሳሪያዎችን ማሰራጨቱን፣ 41 አገሮች የመመርመር አቅም ማጎልበታቸው፤ የምርመራ መሳሪያ (ኪት) አቅርቦት ማሟላታቸውንና ማዕከሉ ተጨማሪ የምርመራ መሳሪያ ግዥ ፈጽሞ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል እንደሚያሰራጭም አስታውቋል።

ለባለሙያዎች ስልጠና መስጠቱን፣ የማዕከሉ ሰራተኞችን በሽታው በበረታባቸው እንደ አልጄሪያና ሴኔጋል አይነት አገሮች ውስጥ ማሰማራቱንና እስከ አሁን ለአባል አገሮቹ ምላሽ የሚሰጡ 24 በጎ ፈቃደኞችን መመልመሉን ገልጸው፤ ወደፊትም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።

ከሲዲሲ በተጨማሪ እንደ ቻይና ያሉ አገሮች የበሽታውን መዛመት ለመግታት በሚደረገው ጥረት ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

እስካሁን የቻይና መንግስት 2 ሺህ የኮሮናቫይረስ መመርመሪያ ቁሶችን ለሲዲሲ ሲያበረክት፣ በሽታውን በመግታት ያላትን ተሞክሮ በቪዲዮ ኮንፈረንስ የእውቀት ስራ አመራር ድጋፍ ማድረጓን አንስተዋል።

በተመሳሳይ አሊባባ የተሰኘው የቻይና ኩባንያ ለህብረቱ አባል አገሮች ከ5 ሺህ በላይ መሳሪያዎችን ለመደገፍ ቃል መግባቱን ጠቅሰዋል።

ዳይሬክተሩ አያይዘውም እጅን አዘውትሮ መታጠብ፣ ከሰዎች ጋር ያለውን ቅርርብ መቀነስ፣ የበሽታው ምልክቶች ሲስተዋሉ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ፣ ሳልና ማስነጠስ ሲከሰት ወደሌሎች ላለማስተላለፍ ጥንቃቄ ማድረግና ሌሎች መንስኤ ከሚሆኑ ድርጊቶች በመቆጠብ ጥንቃቄ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም