ኢትዮጵያ ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት ጃፓን ትደግፋለች - አምባሳደር ዳይሱኬ ማትሱናጋ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት ጃፓን ትደግፋለች - አምባሳደር ዳይሱኬ ማትሱናጋ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 10/2012 (ኢዜአ)ኢትዮጵያ ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት ጃፓን ከጎን በመሆን እንደምትደግፍ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ዳይሱኬ ማትሱናጋ አስታወቁ።
ቫይረሱን ለመከላከልና መፍትሔ ለማግኘት ሁለቱ አገሮች በጋራ በመሆን እንደሚሰሩም ገልጸዋል።
አምባሳደር ዳይሱኬ በኢትዮጵያ በተደረገላቸው ምርመራ ሶስት ጃፓናውያን ዜጎች በቫይረሱ መያዛቸውን አስታውሰዋል።
ዜጎቹ በፍጥነት እንዲያገግሙ ድጋፍ እያደረጉ ላሉ አካላት አምባሳደሩ ምስጋና ማቅረባቸውን በኢትዮጵያ የጃፓን ኤምባሲ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
ኤምባሲው የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መመሪያን ተከትሎ የዜጎቹን ሁኔታ እየተከታተለና ከኢንስቲትዩቱ ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
''የገጠመንን ፈተና በልበ ቅንነትና በቁርጠኝነት አጥብቀን እንታገለዋለን'' ሲሉ አምባሳደሩ ተናግረዋል።
እስከዛሬዋ ቀን ድረስ በኤምባሲውና በአፍሪካ ህብረት የጃፓን ልዑካን ውስጥ በኮሮናቫይረስ የተያዘና የቫይረሱን ምልክቶች ያሳየ ሰው እንዳልተገኘM አመልክተዋል።
''የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ በአሁኑ ሰአት ለዓለም ከባድ ፈተና የሆነውን ኮሮናቫይረስ ለመከላከል ጥረት እያደረጉ እንደሆነና ይሄንኑ ጥረት ጃፓን ከኢትዮጵያ ጎን በመሆን ትደግፋለች'' ብለዋል አምበሳደር ዳይሱኬ።
ሁለቱ አገሮች በጋራ ሆነው ቫይረሱን ለመከላከል በሚያከናውኑት ተግባር በቅርብ ጊዜ ውጤት ማምጣት ይችላሉ ብለው እንደሚያምኑም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያና ጃፓን የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ያላቸው ወዳጅነትና ግንኙነት እየጎለበተና እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
በረጅም ጊዜ ወዳጅነትና የጋራ መተማመን ላይ መሰረት አድርጎ ግንኙነቱ ወደፊትም ይበልጥ እንደሚያድግና እንደሚጠናከር ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።