ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና ሞሮኮ ኢኮኖሚያዊ ትስስር በፍጥነት እያደገ መምጣቱን አምባሳደር የሺ ታምራት ተናገሩ

ሞሮኮ ሚያዝያ 27/2010 የኢትዮጵያና ሞሮኮ ኢኮኖሚያዊ ትስስር በፍጥነት እያደገ መምጣቱን በሞሮኮ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሺ ታምራት ተናገሩ። በሞሮኮ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሺ ታምራት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት ሁለቱ አገራት በኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላቸው ግንኙነት ተጨባጭ ለውጥ እያሳየ ነው። ሁለቱ አገራት ግንኙነታቸውን በአዲስ መልክ ከጀመሩ ገና ሁለት አመታትን ያስቆጠሩ ቢሆንም በርካታ የሞሮኮ ኩባንያዎች  ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ይገኛሉ። "በኢትዮጵያና በሞሮኮ መካከል ከተፈረሙት የሁለትዮሽ ስምምነቶችና ወደ ኢትዮጵያ ካመሩት ኢንቨስተሮች መካከል ስንቶቹ ወደ ተግባር ገብተዋል የሚለውን ሚሲዮናችን ይከታተላል" ያሉት አምባሳደሯ ብዙዎቹ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውንም ገልፀዋል። ኢትዮጵያ በአብዛኛው የማዳበሪያ ምርትን ከሞሮኮ የምታስገባ ሲሆን በመካከላቸው ያለው የንግድ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያን የወጭ ንግድ እንዲያሳድግ ምቹ ሁኔታዎች እየፈጠሩ መሆናቸውንም ገልፀዋል። በተለይም ቡናና የቅባት እህሎች በሞሮኮ ከፍተኛ ተፈላጊነት አላቸው ያሉት አምባሳደሯ ምርቶቹ ወደ ውጭ የሚላኩበት የትራንስፖርትና ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎች እየተሟሉ ይገኛሉ ብለዋል። በሞሮኮ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የቱኒዚያን የሁለትዮሽ ግንኙነትም ለማጠናከር ወክሎ የሚሰራ ሲሆን "ሞሮኮና ቱኒዚያ ያለፉበት የእድገት ደረጃ ለኢትዮጵያ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥና ሊወሰድ የሚገባው ነው" ሲሉም አምባሳደሯ ተናግረዋል። በተለይም ኢትዮጵያ አሁን ለጀመረችው የኢንዱስትሪ ፓርክና ዘመናዊ ግብርና ስራዎች ከሰሜን አፍሪካ አገራት ጥሩ ልምድ እንደምታገኝ ገልጸዋል። ኢትዮጵያና ሞሮኮ በግብርናው ዘርፍ ያላቸው ትብብር ከፍተኛ ሲሆን ለዚህም በኢትዮጵያ የተጀመሩት የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ፣የመስኖ ማሰልጠኛ ተቋማትና በቅባት እህሎች፣በምግብ ማቀነባበርና ሌሎች ዘርፎች እያደረጉት ያለው የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ተጠቃሽ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም