ቀጥታ፡

የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተከናውነዋል….አቶ ኦርዲን በድሪ

ሀረር፤ መጋቢት 10/2012(ኢዜአ)በሐረሪ ክልል ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ የተቋቋመው ማዕከል የግብዓት እጥረት እንዳይገጥመው እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለጹ።

ርዕሰ-መስተዳደሩ ከካቢኔ አባላት ጋር በክልሉ ከኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ለሚደረግ ቅድመ ዝግጅት የተቋቋመውን ማዕከል ዛሬ በጎበኙበት ወቅት እንደገለጹት፤ በክልሉ ቫይረሱን ለመከላከልና ከተከሰተም ጉዳት ሳያደርስ በቁጥጥር ስር ለማዋል እንዲቻል ግብረ-ሃይል ተቋቁሞ እየተሰራ ነው።

የክልሉ መንግስትም ለህክምና አስፈላጊ ግብዓት በማሟላትና የሰው ኃይል እጥረት እንዳይፈጠር በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ለምስራቅ የሀገሪቱ ክፍል እንዲያገለግል የተቋቋመው ማዕከል ውጤታማ ስራ እንዲያከናውን ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግለትም ጠቁመዋል።

"በአሁኑ ወቅት ዋና ተግባራችን መሆን ያለበት ህዝባችን በኮሮና ቫይረስ እንዳይጠቃ እና ከተያዘም ቶሎ እንዲያገግም ማድረግ ነው" ያሉት ርእሰ-መስተዳድሩ ህብረተሰቡም የመከላከል ስራውን ማጠናከርና በተለይም ደግሞ ንጽህናን በመጠበቅ ንክኪዎችን ማስቀረት እንደሚገባ ገልጸዋል።

"የክልሉ ጤና ቢሮም ለማህበረሰቡ እያከናወነ የሚገኘውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ማጠናከር ይገባዋል" ሲሉ ተናግረዋል።

የማዕክሉ አስተባባሪ እና የድንገተኛና ጽኑ ህሙማን ስፔሻሊስት ዶክተር ናታን ሙሉብርሃን በበኩላቸው "በአሁኑ ወቅት ባለሙያው አስፈላጊውን ስልጠና በመውሰድና ለማዕከሉ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በማሟላት ወደ ስራ እንዲገባ ተደርጓል"ብለዋል።

"ሆኖም በአሁኑ ወቅት ለማዕከሉ የሲቲ ስካንና አልትራ ሳውንድ መሳሪያዎች ማሟላትና የውሃ አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት መስራት ይገባል" ሲሉ ተናግረዋል።

"ማዕከሉ ከሐረሪ ክልልና ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመቀናጀትና ለምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል ምርመራና ህክምና መስጠት የሚያስችል ነው" ያሉት ደግሞ የህይወት ፋና ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ ዶክተር ኢብሳ ሙሳ ናቸው።

በማዕከሉ ሊኖሩ የሚገባቸው ተጨማሪ የህክምና መሳሪያዎችን ለማሟላት ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በጉብኝቱም ርዕሰ መስተዳድሩን ጨምሮ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ሰለሞን ኩቹ እንዲሁም ሌሎች የካቢኔ አባላትና የሴክተር መስሪያ ቤት ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም