ቀጥታ፡

የጤና ባለሙያዎችን ምክር በመተግበር የኮሮና ቫይረስን መከላከል ይገባል…የድሬዳዋ ከተማ ምክትል ከንቲባ

ድሬዳዋ ፣መጋቢት 10/2012 (ኢዜአ) ህብረተሰቡ የጤና ባለሙያዎችን ምክር በአግባቡ በመተግበር በተረጋጋ መንገድ እራሱን ከኮሮና ቫይረስ እንዲጠብቅ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አህመድ መሐመድ ቡህ ጥሪ አቀረቡ።


ወቅታዊ ሁኔታውን መነሻ በማድረግ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ጥብቅ ክትትል እየተደረገ መሆኑንም ከንቲባው ገልጸዋል።

ከንቲባው ከካቢኔ አባሎቻቸው ጋር እጃቸውን በሳሙና በመታጠብ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት ህብረተሰቡ የእጅ መጨባበጥ ሰላምታን ትቶ የባለሙያዎችን ምክር በመተግበር የቫይረሱን ስርጭት መከላከል ይኖርበታል።

በተረጋጋ ሁኔታ የመከላከሉን ስራ በአግባቡ በመተግበር የቫይረሱን ስርጭት በቀላሉ መከላከል እንደሚቻል የገለጹት ምክትል ከንቲባው ለዚህም በሁሉም መስክ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን አመልክተዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን አለም አቀፍ ወረርሽኙን ተገን በማድረግ በህክምና መገልገያዎችና በፍጆታ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑንም ምክትል ከንቲባው አስታውቀዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ፉአድ ከድር በበኩላቸው የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተ ጀምሮ ለባለሙያዎች፣ በየደረጃው ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሥልጠና መሰጠቱንና የግንዛቤ ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።

"ድሬዳዋ ከጎረቤት ጅቡቲና ከተጎራባች ክልሎች ጋር በንግድና በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች የሰዎች መስተጋብር የሚበዛበት በመሆኑ የተጠናከረ የመከላከል ተግባር እየተከናወነ ይገኛል" ብለዋል።

በእስከ አሁኑ ሒደትም ምልክቱ የታየበት አንድ ግለሰብ ናሙና ወደ አዲስ አበባ ተልኮ በምርመራ ነጻ መሆኑ መረጋገጡን ገልፀዋል።

"ቫይረሱ ድንገት ቢከሰት እንኳን ከተዘጋጀው የነምበር ዋን የማቆያ ስፍራ በተጨማሪ ሌሎች ስፍራዎችን የማዘጋጀት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል" ያሉት ዶክተር ፉአድ በጤና ተቋማት አስፈላጊ የህክምና መገልገያዎችና የመከላከያ ቁሳቁሶች መሟላታቸውንም ተናግረዋል ፡፡

"ህብረተሰቡ በብዛት በሚዘዋወርበት አካባቢ ስለቫይረሱ መከላከያዎች በስፋት የማስተማር ሥራ ከመስራት ጎን ለጎን ሣሙና በሁሉም ቀበሌዎች በማሰራጨት እጆችን የመታጠብ ተግባር ባህል እንዲሆን ይሰራል" ብለዋል።

በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ የመንግስት ተቋማት በሙሉና ሰው በብዛት በሚሰበሰብባቸው አካባቢዎችም እጅን በሳሙና የመታጠብና የማስታጠብ ተግባር ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም