ማኅበሩ ለአረጋዊያንና አቅመ ደካሞች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ማኅበሩ ለአረጋዊያንና አቅመ ደካሞች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ ጀመረ
አዲስ አበባ ፣መጋቢት 10/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መሰረታዊ ብረታ ብረትና ኢነጂነሪንግ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር የኮሮናን ቫይረስ ለመከላከል ለአረጋዊያንና አቅመ ደካሞች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ ጀመረ።
ማኅበሩ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸውን የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች የሚያቀርበው መንግሥት በሽታውን ለመከላከል ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ ነው።
የማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሊቀ መንበር አቶ በትሩ ወልደሃና እንደተናገሩት፤ ለቫይረሱ ተጋላጭ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ይደርጋል።
በሥሩ ያሉትን አምራቾች በማስተባበር የተጠቀሰውን ድጋፍ የሚያደርገው በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንደሆነም ገልጸዋል።
ተሽከርካሪ ያላቸው የማኅበሩ አባላት በአዲስ አበባ የትራንስፖርት እጥረት በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች ድጋፉን እንዲያደርሱም ጠይቀዋል።
የማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሰለሞን ሙሉጌታ በበኩላቸው ማኅበሩ አባላቱን በማስተባበር ሶፍትና ሳሙና ለመለገስ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
ድጋፉ በተለያዩ ማዕከላት የሚገኙ አቅመ ደካማ ወገኖችን ተደራሽ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።
በዛሬው ዕለትም ማኅበሩ 100 ሺህ ብር የሚገመት ደረቅና ፈሳሽ የልብስና የገላ ሳሙና እንዲሁም ሶፍት ለመቄዶኒያ አረጋዊያንና አዕምሮ ሕሙማን ማዕከል አበርክቷል።
በአገር አቀፍ ደረጃ 75 አምራቾችን በአባልነት የያዘው ይህ ማኅበር የተቋቋመው በ1999 ዓ.ም ነው።