ሙስሊሙ ህብረተሰብ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ሙስሊሙ ህብረተሰብ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ መጋቢት 10/2012 (ኢዜ አ) ሙስሊሙ ህብረተሰብ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚደረገውን እንቅስቃሴ እንዲደግፍ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጥሪ አቅርቧል፡፡
ምክር ቤቱ በመግለጫው በዓለም አቀፍ ደረጃ አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የኮሮናቫይረስ ስርጭት ለመከላከል ሙስሊሙ አቅም ለሌላቸው ዜጎች የመከላከያ ቁሳቁሶችን በማቅረብ የበኩሉን ሀላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቋል።
ማህበረሰቡ አቅም ለሌላቸው ዜጎች እንደ ሳሙናና አልኮል ያሉ ንፅህና መጠበቂያዎችን በማቅረብ ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅበት ተገልጿል፡፡
በዚሁ መግለጫ ላይ የምክር ቤቱ የሀጅ እና ኡምራ ዘርፍ ሃላፊ ዶክተር ጄይላን ገለታ እንደጠቆሙት፤ ህብረተሰቡ የሚሰጠውን ምክር በመቀበልና ተግባራዊ በማድረግ ራሱንና ቤተሰቡን መጠበቅ አለበት፡፡
ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የሚያግዝ ማሳሰቢያና ትምህርት በየመስጊዱ እንደሚሰጥ አመልክተው፤ ሙስሊሙ የዘወትር ፀሎት ከማድረግ ጎን ለጎን የግልና የአካበቢ ንፅህናውን እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በተለይ በመስጊዶች አካባቢ የሚደረጉ ዘለግ ያሉ ቆይታዎችን በማሳጠርና በቀን አምስት ጊዜ የሚደረገውን የንፅህና አጠባበቅ ጊዜን በመጨመር በሽታውን መከላከል እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በምክር ቤቱ የክልልና ድርጅት ጉዳዮች ሀላፊ ሼክ ሰኢድ አህመድ በበኩላቸው ''ሙስሊሙ ህብረተሰብ አቅም ያጡ ወገኖቹን የመደገፍ ግዴታ እንዳለበት በማወቅ ራሱንና አካባቢውን ከበሽታው ለመከላከል በሚደረጉ ጥረቶች መሳተፍ አለበት'' ብለዋል፡፡
ችግሩን ምክንያት በማድረግ አላስፈላጊ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች የሚሰሩት ተግባር ሀጢአት መሆኑን ተገንዝበው ከድርጊታቸው ሊታቀቡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
''በችግር ወቅት መከላከያ መንገዶችን መከተል ተገቢ ነው'' ያሉት ሼህ ሰኢድ፤ የበሽታውን ምንነትና የሚያስከትለውን ጉዳት በተገቢው መንገድ ማስተማር እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
የምክር ቤቱ የመስጊድ አወቃቀር ዘርፍ ሀላፊ ሼክ ሙሃመድ ሀምዲን ሙስሊሙ ወደ መስጊድ በሚመጣበት ወቅት የራሱን መስገጃ ይዞ በመምጣትና የሚገለገልባቸው የንጽህና መጠበቂያ እቃዎቹን በአግባቡ እንዲይዝ አሳስበዋል።
በየመስጊዶቹ ደጃፍ የንጽህና መጠበቂያ መሳሪያዎችን በማቅረብ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ የሚሆንበት አሰራር መዘርጋቱን የተናገሩት ሼክ ሙሃመድ፤ ባለሀብቶችና በጎ አድራጊ ግለሰቦች እንዲተባበሩም ጠይቀዋል፡፡
የበሽታው ሁኔታ ስጋት ቢያሳድርም የመስጊድ ስግደቶችን የሚያስቀር አለመሆኑን ተናግረው አሳሳቢ ደረጃ ላይ ከደረሰ ግን ስግደቶች በቤት ውስጥ ተወስነው የሚቆዩበት ሁኔታ ሊመቻች እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡