በባሌ ሮቤና በጅማ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ ነጋዴዎች ላይ አርምጃ ተወሰደ - ኢዜአ አማርኛ
በባሌ ሮቤና በጅማ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ ነጋዴዎች ላይ አርምጃ ተወሰደ
ጎባ ጅማ፥ መጋቢት 10/2012 (ኢዜአ) - በባሌ ሮቤና በጅማ ከተሞች ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መውሰዳቸውን የከተሞቹ ንግድ ጽሕፈት ቤቶች ገለጹ።
በባሌ ዞን ሮቤ ከተማ በመሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ ያለአግባብ ዋጋ ጨምረው ሲሸጡ የነበሩ ሰባት ነጋዴዎች የንግድ ቤታቸው እንዲታሸጉ ማድረጉን የከተማ አስተዳደሩ ንግድ ጽሕፈት ቤት ገልጿል ።
የኮሮና ቫይረስ በአገሪቱ መከሰቱን ተከትሎ አላግባብ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር የገበያ ማረጋጋት ግብረ ኃይል ተቋቋሞ ወደ ሥራ መግባቱ ተጠቁሟል።
በነጋዴዎች ላይ እርምጃው የተወሰደው ምክንያት የሌለው የዋጋ ጭማሪ አድርገው በመገኘታቸው መሆኑን የከተማዋ ንግድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ገነት ብርሃኑ ለኢዜአ ገልጸዋል።
ከኅብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሠረት ግብረ ኃይሉ ባደረገው ቅኝት አለአግባብ ዋጋ ጨምረው ሲሸጡ የተገኙ ሰባት የንግድ ተቋማት እንዲታሸጉ ተደርጓል።
ነጋዴዎቹ በአካባቢው ሦስት ሺህ ብር ሲሸጥ የነበረውን አንድ ኩንታል ጤፍ እስከ 3ሺህ 500 ብር፣ አሥር ብር ይሸጥ የነበረውን ለስላሳ መጠጥ እስከ 18 ብር የሸጡ ሲሆን ነጭ ሽንኩርትን ጨምሮ በሌሎች አትክልትና መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።
በቀጣይም ተመሳሳይ ተግባር በሚፈጽሙ ነጋዴዎች ላይ የንግድ ፍቃድ በመሰረዝ በሕግ አግባብ ለመጠየቅ የሚያስችል የተጠናከረ እርምጃ እንደሚወስድ ገልጸዋል፡፡
ኅብረተሰቡ መንግሥት የሚሰጠውን መረጃ በመከታተል ራሱን ከቫይረሱ እንዲከላከልና ሕገወጦችን በማጋለጥ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል።
በሌላ በኩል ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን የጅማ ከተማ ንግድ ጽህፈት ቤት አስታወቋል።
የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ የዚድ አባገሮ ለኢዜአ እንደገለጹት በጅማ ከተማ የሚገኙ አንዳንድ ነጋዴዎች ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እንዳያደርጉ አስቀድሞ የግንዛቤ ማስጨበጫና የምክር አገልግሎት ተሰጥቷል።
ሆኖም ግን የተሰጣቸውን ምክር ችላ በማለት የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 20 ነጋዴዎች ላይ ድርጅቶቻቸውን የማሸግ እርምጃ ተወስዷል።
እርምጃ ከተወሰደባቸው የንግድ ተቋማት መካከል ዳቦ ቤቶች፣ የእህል ንግድ ድርጅቶች፣ የአትክልት መሸጫ መደብሮች፣ መድኃኒት ቤቶች፣ የጅምላና የችርቻሮ ሱቆች እንደሚገኙበት ተናግረዋል።
በከተማው የግብርናና የፋብሪካ ምርቶች እጥረት የሌለ በመሆኑ ነጋዴዎች ምንም ዓይነት የዋጋ ጭማሪ ማድረግ እንደሌለባቸው አስጠንቅቀዋል።