ቀጥታ፡

የግድቡ ግንባታ ከፍጻሜ ለማድረስ ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን... የማይጨውና የአክሱም ነዋሪዎች

ማይጨው /አክሱም ኢዜአ መጋቢት 10/12 ዓ/ም  የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ከዳር ለማድረስ ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ የማይጨውና የአክሱም ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ ።

የታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተበሰረበት ማግስት ጀምሮ ላለፉት ስምንት ዓመታት ያለማቋረጥ በየዓመቱ ቦንድ በመግዛት እገዛ እያደረጉ መሆናቸውን የከተማው ነዋሪ አቶ ሐጎስ ገብረስላሴ ተናግረዋል።

አቶ ሐጎስ እስከ አሁን ድረስ በራሳቸው እና በልጆቻቸው ስም ለግድቡ ግንባታ ከ80 ሺህ ብር በላይ ቦንድ መግዛታቸውንም አስታውሰዋል።


"አገራት የሚበለጽጉት በውስጣቸው ያለውን ነዳጅ ተጠቅሞ ነው፣የኛ ኢትዮጵያውያን ሀብት ደግሞ ውሃ ነው። ስለሆነም የራሳችንን ሀብት በአግባቡ አልምተን ጥቅም ላይ ለማዋል የጀመርነውን ግድብ እጅ ለእጅ ተያይዘን ልናጠናቅቀው ይገባል " ብለዋል።


የታላቁ የኢትዮጰያ ህዳሴ ግድብ ለሁሉም ኢትዩጵያውያን የሚጠቅም እስከሆነ ድረስ ከገንዘብ ጀምሮ እሰከ ህይወት መስዋዕትነት ድረስ ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።


ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ከሚያገኙት ደመወዝ እየተቆረጠ ለአባይ ግድብ ግንባታ ድጋፍ መስጠታቸውን የሚናገሩት ደግሞ አቶ ሀይለኪሮስ ገብረ ናቸው።


አሁንም ከመንግሥት ጎን በመቆም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ገብረትንሣኤ ገብረፃዲቅ በበኩላቸው በራሳቸውና በቤተሰቦቻቸው ስም ከ20 ሺህ ብር በላይ ቦንድ በመግዛት ለህዳሴ ግድብ የዜግነት ድርሻቸውን በኃላፊነት መንፈስ እንደተወጡ ገልፀዋል ።


በህዳሴው ግድብ እኩል ተጠቃሚ በመሆናችን ሁላችንም የድርሻችንን መወጣት እንዳለብን ስለምገነዘብ ድጋፌን አጠናክሬ እቀጥላለሁ ብለዋል ።

በተመሳሳይ ሁኔታ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ላይ የሚታዩ የውጭ ጣልቃ ገብነቶችን ለማክሰም አንድነታችንን አጠናክረን  ግንባታውን ከፍፃሜ ለማድረስ በቁርጠኝነት መነሳሳት አለብን ሲሉ የአክሱም ከተማ ነዋሪዎች ገልፀዋል ።

በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚ ምሁር ዶክተር አብረሀ ገብሩ በሰጡት አስተያየት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ባሻገር ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ትርጉሙ ከፍ ያለ ነው ብለዋል።

የግድቡን ግንባታ ለማፋጠን የሚታየውን ህዝባዊ መነሳሳት ፣ አንድነትና ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል ።

ታላቁ ህዳሴ ግድብ የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ማህበራዊ ግንኙት በማጠናከር የኢትዮጰያ ህዝብ የእድገት ፍላጎት የሚመልስ በመሆኑ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ምሁሩ አሳስበዋል ።

በአክሱም ከተማ የክንደያ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ፉአድ ዓብደልዓዚዝ እንደተናገረው ለግድቡግንባታ በሶሰትጊዜ የ6 ሺህ ብር ቦንድ ግዥ በመፈፀም አሻራውን አኑሯል ።

የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሀገራዊ መግባባት የሚያጠናክርና የህዝብ ለህዝብ ትስስር ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያሸጋግር በመሆኑ ደጋፉን አጠናክሮ ለመቀጠል ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም