ቀጥታ፡

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፉ የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ተዘጋጀ

መቀሌ ፣መጋቢት 10/2012 (ኢዜአ ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የተጀመረበት ዘጠነኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በትግራይ ክልል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ተዘጋጀ።
የክልሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ኃይለኪሮስ ጠዓመ ለኢዜአ እንደገለጹት ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ እንዲውል የተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ መረሃ ግብሩ ለአስር ቀናት የሚቆይ ነው።

በመረሃ ግብሩ መሰረት ከዛሬ ጀምሮ ለአስር ቀናት በሚኖረው ቆይታ የቦንድ ግዥና በፋይናንስ ተቋማት መካከል የስፖርት ውድድር ይደረጋል።

በሽሬ እንዳስላሴና ማይጨው ከተሞች  ደግሞ በክልል ደረጃ የፓናል ውይይት እንደሚካሄድ ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

"ግብፅ የሚያስፈልጋትን ውሃ ለማቆር እየተሯሯጠች ባለችበት ወቅት ኢትዮጵያዊያን የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ የማንሯሯጥበት ምክንያት የለም" ብለዋል።

የክልሉ ህዝብ በተያዘው ዓመት ከአንድ ሚሊዮን 900 ሺህ ብር  በላይ የቦንድ ግዥ መፈፀሙን አመልክተው ህዝቡ ዛሬም እንደ ትናንቱ ለግድቡ ድጋፉን  አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

ምሁራን ህዝቡ ሲያደርገው የነበረውን የነቃ ተሳትፎ እንዲቀጥል በማነሳሳት የድርሻቸውን እንዲወጡም አቶ ኃይለኪሮስ  መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በትግራይ ማዕከላይ ዞን የዓብይ ዓዲ ነዋሪ ታጋይ ኪሮስ አስፋው በሰጡት አስተያየት "ግድቡ  እስኪጠናቀቅ ድረስ ቦንድ መግዛት አላቋርጥም" ብለዋል።

800 ብር ወርሃዊ ደመወዝ  እየተከፈላቸው በነበሩበት ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ በየወሩ በግማሽ ደመወዛቸው ቦንድ በመግዛት ሲደግፉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

ድጋፉን ሳያቋርጡ እንደቀጠሉበትና አሁን እየተከፈላቸው ካለው አምስት ሺህ ብር ወርሃዊ ደሞዝ ግማሹን በየወሩ ቦንድ እየገዙበት መሆኑንም ገልጸዋል።

''የህዳሴ ግድቡ የኢትዮጵያውያን የጋራ ሃብት ነው'' ያሉት ታጋይ ኪሮስ ፤ በግድቡ ዙሪያ የተጀመረው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

 የህዝቡ ተሳትፎ እንዲጎለብት የማነሳሳት ስራ እየተሰራ አይደለም ያሉት ታጋይ ኪሮስ አሁን በግድቡ ዙሪያ የተጀመረው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። 

ለሰባተኛ ጊዜ የቦንድ ግዥ እንደፈጸሙ የተናገሩት ደግሞ በደቡባዊ ምስራቅ ዞን የሰሃርቲ ሳምረ ወረዳ ነዋሪ አቶ ወልደምህረት ነጋ ናቸው።

የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚያደርጉትን ድጋፍ እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

የትግራይ ክልል ህዝብ ታላቁ የኢትዮጵያ  ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ አንስቶ እስካሁን  ከ650 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ከማስተባበሪያው ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመላክታል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም