ቀጥታ፡

አልኮል ለንጽህና መጠበቂያ መዋሉን ተከትሎ እጥረት አጋጥሟል

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 10/2012 ( ኢዜአ) አልኮል የኮሮና ቫይረስን ( ኮቪድ-19) ለመከላከል ለንጽህና መጠበቂያነት መዋሉን ተከትሎ እጥረት እንዳጋጠማቸው የጤና ተቋማትና ሌሎች ድርጅቶች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ በበኩሉ እጥረቱ በፍላጎትና በአቅርቦት አለመጣጣም የተከሰተ በመሆኑ ምርቱን ለመጨመር እየሰራሁ ነው ብሏል።

ሆስፒታሎች፣ መድሃኒት ቤቶች፣ ቀይ መስቀል፣ ባንኮች፣ ማረሚያ ቤቶችና ሌሎች ተቋማት የአልኮል ፍላጎታቸውን ለፋብሪካው ሲያቀርቡ ኢዜአ በቦታው ተገኝቶ ተመልክቷል።

ከነዚህ ተቋማት መካከል ከሆስፒታል፤ ከመድሃኒት ቤትና ከማረሚያ ቤት የመጡ አስተያየት ሰጪዎች እንደገለጹት በጥያቄያቸው መሰረት አልኮል እያገኙ ባለመሆኑ አገልግሎታቸው ላይ ጫና ፈጥሯል። 

ከአዲስ የልብ ሕክምና ሆስፒታል የመጡት ወይዘሮ ሃይማኖት ኃይለማርያም  በፋብሪካው ውስጥ አልኮል አለ ማግኘታቸውን ገልጸው ፤ በዚህም ሳቢያ ህመምተኞችን ለማስተናገድ እንደሚቸገሩ ተናግረዋል። 

አልኮል ለመውሰድ ለሶስት ቀናት ወደ ፋብሪካው መመላለሳቸውንና ከፍተኛ እጥረት መኖሩን የተናገሩት ደግሞ ከጁዲስ ፋርማሲቲካልስ የመጡት አቶ ኢሳያስ ሱቱማ ናቸው።   

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ምክትል ኢንስፔክተር ረታ አዶ በበኩላቸው በፋብሪካው ውስጥ አልኮል የለም በመባሉ እየተመለስኩ ነው ብለዋል። 

በሌላ በኩል ከአዲስ አበባ ቀይ መስቀል የመጡት አቶ አለሙ ለገሰ ለሚሰጡት የአምቡላስን አገልግሎት የሚያስፈልጋቸውን አልኮል በጠየቁት መሰረት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ኮኮቤ ቁምቢ ቀደም ሲል ለሆስፒታሎችና ሌሎች ተቋማት ይሰራጭ የነበረው የአልኮል ምርት የኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ ለንጽህና መጠበቂያ ጥቅም ላይ በመዋሉ ፍላጎቱ መጨመሩን ተናግረዋል።

ድርጅቱ በቀን እስከ አንድ ሺህ ሊትር አልኮል ቢያመርትም ካለው ፍላጎት ጋር ሊመጣጠን ስላልቻለ ምርቱን ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የምርት አቅርቦቱ እስኪጨምር ድረስ ሕጋዊ ንግድ ፈቃድ ያላቸው፣ የመንግስት ተቋማት፣ ሆስፒታሎች፣ ባንኮችና ሌሎች ከሕዝብ ጋር ንክኪ ያላቸው ድርጅቶች በጥያቄያቸው መሰረት በቅደም ተከተል ይስተናገዳሉ ብለዋል።

አልኮል በሕክምና ተቋማት ለሕክምና ቁሳቁስ ማፅጃ፣ ለሕሙማን ሕክምና ለመስጠትና ለሌሎችም አገልግሎቶች ይውላል።

የኮሮና ቫይረስ በንክኪ የሚተላለፍ ሲሆን ሳሙና እና ውሃ፣ አልኮልና ሌሎች የንጽህና መጠበቂያዎችን በመጠቀም መከላከል እንደሚቻል የጤና ባለሙያዎች ይመክራሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም