የንግዱ ማኅበረሰብ በበለጠ አገራዊ ስሜት ከሕዝብና ከመንግስት ጎን እንዲቆም ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የንግዱ ማኅበረሰብ በበለጠ አገራዊ ስሜት ከሕዝብና ከመንግስት ጎን እንዲቆም ተጠየቀ
አዲስ አበባ መጋቢት 10/2012 (ኢዜ አ) በአገሪቷ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንዳያስከትል የንግዱ ማኅበረሰብ ከየትኛወም ጊዜ በላቀ አገራዊ ስሜት ከሕዝብና ከመንግስት ጎን እንዲቆም ተጠየቀ።
የንግዱ ማኅበረሰብ ማንኛውንም የንግድ እቃ፣ ሸቀጥ፣ መሰረታዊ የፍጆታ እቃ፣ ምርትና አገልግሎት ላይ ምንም አይነት የዋጋ ጭማሪ እንዳያደርግ የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጥሪ አቅርቧል።
መሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ ዋጋ ሳይጨምር፣ የጥራት ደረጃ ሳያጓድል፣ የሚዛን መስፈሪያ መሳሪያዎችን ሳያስተጓጉል፣ ባዕድ ነገር ሳይቀላቅልና ምርት ሳይደብቅ በማቅረብ የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣም አሳስቧል።
ነጋዴዎች የሕዝቡ አካል እንደመሆናቸው የተከሰተው የጤና ችግርም የጋራ መፍትሄና ትብብር የሚሻ በመሆኑ ፍትሃዊ የንግድ አሰራር በመተግበር ከሕዝብና ከመንግስት ጎን በመቆም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ እንደሚገባም አስገንዝቧል።
የኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ በአዲስ አበባ በተለያዩ ሸቀጦች ላይ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ያለአግባብ ለመበልፀግ ሲሰሩ በተገኙ 188 ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን የመዲናዋ ንግድ ቢሮ መግለጹ ይታወቃል።
በሸቀጦች ላይ እየተደረገ ያለውን ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ የሚቆጣጠር ግብረኃይል አቋቁሞ ይህን የሚያደርጉ ነጋዴዎችን የመከታተል፣ የመቆጣጠርና ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ የመውሰድ ስራውን ማጠናከሩንም የገለፀው በዚሁ ሳምንት ነው።