የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዶ/ር ካትሪን ሐምሊን ሞት የተሰማውን ሃዘን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዶ/ር ካትሪን ሐምሊን ሞት የተሰማውን ሃዘን ገለጸ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 10/2012(ኢዜአ) የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዶ/ር ካትሪን ሐምሊን ሞት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ገለጸ።
ሚኒስቴሩ ለስራ ባልደረቦቻቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው እና ለቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናትን ተመኝቷል።
በትውልድ አውስትራሊያዊ የሆኑት ዶ/ር ካትሪን ሐምሊን ፌስቱላ ኢትዮጵያ የተባለ ግብረሰናይ ድርጅት በማቋቋም ከ60 ዓመት በላይ የፌስቱላ ህክምናን ሰጥተዋል።
በዚህ የበጎ አድራጎት ተግባራቸው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሴቶችን ከፊስቱላ ችግር ነጻ አውጥተዋል ብሏል።
ዶ/ር ካትሪን ሐምሊን በዚህ በጎ ተግባራቸው የኢትዮጵያ የክብር ዜግነት እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ የክብር ዶክትሬት ተበርክቶላቸዋል፡፡
ዶ/ር ካትሪን ሐምሊን ለኢትዮጵያ ህዝብ ባበረከቱት በጎ ስራቸው ለዘላለም ሲታወሱ ይኖራሉ ሲል ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ሀዘኑን ገልጿል።