"ግብጽ ኢትዮጵያን ልታበረታታ እንጂ ልትከስ አይገባም" - ኢዜአ አማርኛ
"ግብጽ ኢትዮጵያን ልታበረታታ እንጂ ልትከስ አይገባም"
መጋቢት 9/2012 (ኢዜአ) "ግብጽ ኢትዮጵያን ልታበረታታ እንጂ ልትከስ አይገባም"- ከግማሽ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ዛሬም ኤሌክትሪክ አላገኘም።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ የወጡ ህግጋት አገራት በመካከላቸው የሚገኘውን ውሃ ፍትሃዊ በሆነ መልኩ መጠቀም እንዳለባቸው ይደነግጋሉ።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያና ግብፅ በአባይ ወንዝ ላይ ያላቸው ተጠቃሚነት እንደማይነጻጸር መረጃዎች ያሳያሉ።
ግብፅ ከጥንት እስከ ዛሬ ወንዙን በበላይነት በመያዝ ለመስኖ፣ ለሃይል ማመንጫና ለትራንስፖርት መጓጓዣነት ጭምር ተጠቅማ የህዝቦቿ አኗኗር መለወጥ ችላለች።
በተቃራኒው ኢትዮጵያ የምንጩ ባለቤት ብትሆንም በአባይ ውሃ ተጠቃሚ ሆና አታውቅም።
ለአብነትም የሁለቱን አገራት የኤሌክትሪክ ሃይል ተደራሽነት ስንመለከት ግብፅ ከፈረንጆቹ 2014 ዓ.ም ጀምራ መቶ በመቶ ያሳካች ሲሆን ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ አሁንም በጨለማ ውስጥ የሚኖር ነው።
ኢትዮጵያ እነዚህን በጨለማ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎቿን ከድህነትና ከጨለማ ለማውጣት የዛሬ ዘጠኝ ዓመት ነበር ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ያኖረችው።
ለዘመናት የኤሌክትሪክ ብርሃን ሳያዩ፣ በእጃቸው እየፈጩ፣ በእንጨት እያበሰሉ የኖሩት ኢትዮጵያዊያን በተስፋ ያላቸውን ሁሉ እያዋጡ ግድቡን እውን ለማድረግ እየታተሩ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ ፍትሃዊ ውሃን የመጠቀም መብቷን በመጠቀም ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የምትገነባው ዜጎቿን ከጨለማ ለማውጣት እንጂ የተፋሰሱን አገራት ዜጎች ለመጉዳት አለመሆኑን በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች።
ግድቡ እውን ሲሆን የአገሪቱን የኤሌክትሪክ ሽፋን ከማሳደግ ጎን ለጎን ለአካባቢው አገራት ተጨማሪ ጥቅሞችን ይዞ እንደሚመጣም ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
ይሁንና ግብጽ ግድቡ ዜጎቿን ችግር ላይ የሚጥል እንደሆነ በመግለጽ የተዛባ አካሄድ ስትከተል ይስተዋላል።
የተለያዩ ታሪካዊ ቦታዎችን እያስጎበኘች ለአምስት አመታት በግብጽ የቆየችው ኢትዮጵያዊቷ ቅድስት ዳግማዊ የአገሪቱ ፖለቲከኞች ወደ ህዝቡ የሚያሰርጹት የተሳሳተ መረጃ ኢትዮጵያዊያን ላይ ጭምር ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ትናገራለች።
በተለይም ኢትዮጵያ ግድቡን የምትገነባው ለቅንጦትና የግብፅን ህዝብ ለመጉዳት እንደሆነ አስመስሎ ለህዝቡ በመሰበኩ ህዝቡ ሁኔታውን በጥርጣሬ እንዲያይ አድርጎታል።
እርሷ ግን በገጠር የኢትዮጵያዊያን አኗኗር ምን እንደሚመስል በማወቋ ብቻም ሳይሆን የግብጻዊያንንም አኗኗር በቅርብ በመመልከቷ ሁለቱን እያነጻጸረች ትናገራለች።
አርቲስት ፋሲል ግርማ በበኩሉ ግብፅ ኢትዮጵያ ሁሉ ነገር እንዳላት አድርጋ እንድትታይ ማድረጓና ግድቡን መገደቧን መቃወሟ ልክ አለመሆኑን ይናገራል።
የግብፅን ህዝብ አኗኗር የምታውቀው ቅድስት የኢትዮጵያዊያንና የግብፅ ህዝቦች ህይወትን ማነጻጸር የሚቻለው አሁን ባለው ሁኔታ ሳይሆን ኢትዮጵያ ከአባይ መጠቀም ስትጀምር ብቻ ነው ትላለች።
አሁን ባለው ሁኔታ የኢትዮጵያዊያ በተለይም የገጠሩ ማህበረሰብ ኑሮ እጅግ አሳዛኝ መሆኑን በመግለጽ።
ግብፆች በኢኮኖሚ ደረጃም የቀይ ባህርን የጨው መጠን በማጣራት ለመስኖ መጠቀም የሚያስችል አቅም፣ የከርሰ ምድር ውሃ የማውጣትም አማራጭ እንዳላቸው መረጃዎች ያሳያሉ።
ይህንን የተመለከተችው ቅድስት አባይ ለግብፅ ብቻ ነው የሚገባው የሚለው አስተሳሰብና ግድቡ መገንባት የለበትም የሚለውን ክርክር ግለኝነት እንጂ አሳማኝ አለመሆኑን፤ ኢትዮጵያ ከግድቡ መጠቀም አለባት የሚል አቋም እንዳላት ትናገራለች።
ኢትዮጵያ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መገንባት ከጀመረች ድፍን ዘጠኝ ዓመታትን ልታስቆጥር የጥቂት ቀናት ጊዜ ቀርተዋታል።
በኢትዮጵያዊያን ሃብት እየተገነባ ያለው ይህ ግድብ በአሁኑ ወቅት 71 ነጥብ 59 በመቶ ላይ ደርሷል።
በዓለም ላይ 261 ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችና ሃይቆች የመሬትን 45 በመቶ በመሸፈን በርካታ አገራትን በማስተሳሰርና የጋራ ተጠቃሚ በማድረግ ይጠቀሳሉ።
በአፍሪካ በርዝመቱ የሚታወቀውና 11 አገራትን አቋርጦ ሜዲትራኒያን ባህር የሚገባው የአባይ (የናይል) ወንዝም ከድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አንዱ ነው።
ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን የሚዳኘው የህግ ማዕቀፍ ደግሞ አገራት ድንበር ተሻጋሪ ወንዝን የላይኛውና የታችኛው ተፋሰስ አገራት ማንንም ጉዳት ላይ በማይጥል መልኩ በመተሳሰብና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንዲጠቀሙ ይደነግጋል።