ቀጥታ፡

ከስደት ተመላሾች በሀገራቸው ሰርተው የተሻለ ገቢ ማግኘት ጀምረዋል

ጎንደር መጋቢት 09/2012 (ኢዜአ) ስደት በቃን ብለን ወደ ሀገራችን ተመልሰን በተለያዩ ስራዎች በመሳተፍ የተሻለ ገቢ ማግኘት ጀምረናል ሲሉ በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ የሚገኙ ከስደት ተመላሾች ተናገሩ፡፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ብሄራዊ ማህበር ዋና ፀሃፊና የቦርድ አባላት በማህበሩ የገንዘብ ድጋፍ በከተማው ከስደት ተመላሾች እራሳቸውን ለማቋቋም እያደረጉት ያለውን ጥረት ጎብኝተዋል፡፡

ሀገራችን ላይ ሰርተን እንድንለወጥ ቀይ መስቀል ባደረገልን የ130 ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ 10 ሆነን በመደራጀት በሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ ስራ ተሰማርተናል ያለችው የደባርቅ ከተማ ነዋሪ ወይዘሪት ጠጅቱ የሽዋሰ ናት፡፡

አሁን ላይ በቀን ከ1ሺህ እስከ 1 ሺህ 200 ብር በመሸጥ የማህበሩ አባላት የንግድ ስራውን አጠናክረን ቀጥለናል ስትል ተናግራለች፡፡

በተደረገላቸው ድጋፍ ተበረታተው በሚያደርጉት የስራ እንቅስቃሴ በሚያገኙት ገቢ የእለት ከእለት ኑሮአቸውን ለመምራት እንዳገዛቸው ገልፃለች።

በሱዳን ሀገር ቆይታ የተመለሰችው ወይዘሮ ዞማ ጀጃው በበኩሏ ማህበሩ ባደረገላቸው የ110 ሺህ ብር ድጋፍ በባልትና ውጤቶች ምርት ሽያጭና በመጠጥ ንግድ 10 ሆነው በመደራጀት ወደ ስራ መግባት መቻላቸውን  ገልፃለች፡፡

በአሁኑ ወቅት በሁለቱም የንገድ ዘርፍ በቀን 1 ሺህ 600 ብር ገቢ በማግኘት ኑሮአቸውን ለመለወጥና ለሌሎችም አርአያ ለመሆን እየሰሩ መሆናቸውን ጠቅሳለች።

በቀይ መስቀል የገንዘብ ድጋፍ 10 ሆነው በመደራጀት በጽህፈት መሳሪያ ንግድ ስራ ተሰማርተው በቀን 400 ብር ገቢ በማግኘት ኑሮአችን ለመምራት ጥረት እያደረግን ነው ያለችው ደግሞ ሌላዋ ከአረብ ሃገር ተመላሽ ወጣት ጮማ መዝገቡ ናት።

ከአረብ ሃገራት አሰቃቂ ኑሮ ተላቃ በመምጣት ከህዝቧና ወገኗ ጋር ሆነና በገቢ ማስገኛ ስራ መሰማራቷም ደስታ እንደፈጠረላት ጠቅሳ ውጤታማ ለመሆንም በርትተው እየሰሩ እንደሆነ ገልፃለች።

በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የጎንደር ቅርንጫፍ የስደት ተመላሾች ማቋቋሚያ ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶክተር ተፈራ አሰፋ በከተማው 115 የሚሆኑ ከስደት ተመላሾችን ለማቋቋም ጥረት በመደረግ ላይ ነው፡፡

ፕሮጀክቱ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ከስደት ተመላሾቹን በንግድ ስራ ክህሎት በማሰልጠን፣ በጽህፈት መሳሪያ፤ በሸቀጣ ሸቀጥ፤ በባልትና ምርት ውጤቶች፤ በእህል ወፍጮና በመዝናኛ የንግድ ዘርፎች እንዲሰማሩ አድርጓል፡፡

ፕሮጀክቱ ለስደት ተመላሾቹ ማቋቋሚያ የሚውል ስድስት ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉንም አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡

የፕሮጀክቱ አስተባባሪ እንደገለጹት በደባርቅ ከተማና ዙሪያው ከ800 በላይ ከስደት ተመላሾች ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም