የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በጥንቃቄ እየተሰራ መሆኑን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በጥንቃቄ እየተሰራ መሆኑን ገለጸ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9/2012 ( ኢዜአ) በባቡር የትራንስፖርት አገልግሎት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ለጥንቃቄ የሚረዱ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አስረታወቀ።
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ስንታየሁ ወልደሚካሄል እንደገለጹት ቫይረሱ እንዳይስፋፋ የጥንቃቄ ስራዎች እየተከናወኑ ነው።
በተለይ በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የትራንስፖርት አገልግሎት ተሳፋሪዎች በቫይረሱ እንዳይያዙ በየፌርማታው በሳሙና እና ውሃ እጃቸውን እዲታጠቡ እየተደረገ ነው።
የባቡሩን ፅዳት በመጠበቅም የቫይረሱ ስርጭት እንዳይኖር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ዶክተር ስንታየሁ ገልጸዋል።
ለባቡሩ ሰራተኞች የእጅ ጓንት፣ የፊት ማስክ እና አኮል በማዘጋጀት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እየተሰራ መሆኑንም እንዲሁ።
የባቡሮች መነሻና መድረሻ ፌርማታዎች በአልኮል እንዲጸዱ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
በ5 ፌርማታዎች ላይ ዛሬ የተጀመረው የእጅ መታጠብ በቀጣይ ቀናት በሁሉም ፌርማታዎች ተግበራዊ ይደረጋልም ነው ያሉት።
በዋና ስራ አስፈጻሚ የሚመራ ሰባት አባላት ያሉት ተከላካይ ግብረ ኃይልም መቋቋሙን ዶክተር ስንታየሁ ገልጸዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የባቡር ትራንስፖርት ተጠቃሚዎችም ቫይረሱን ለመከላከል ኮርፖሬሽኑ እያከናወነ ያለውን ተግባር አድንቀዋል።
ቫይረሱ በንክኪ የሚተላለፍ በመሆኑ እጃችንን እንድንታጠብ መደረጉ የሚያስደስት ነው ሲል ወጣት አብረሃም ጫላ ገልፆልናል።
ሌላው የባቡር ትራንስፖርት ተጠቃሚ አቶ በለጠ ጉርሙም ኮርፖሬሽኑ እያደረገ ያለው ቅድመ ጥንቃቄ ሌሎች አገልግሎት ሰጭ ተቋማትንም የሚያበረታታ ነው ብለዋል።
በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት በቀን በአማካይ ከ110 ሺህ በላይ ተሳፋሪዎች እንደሚገለገሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።