ቀጥታ፡

ሴቶች ለህዳሴ ግድብ የሚያደርጉት ድጋፍ እንዲጠናከር ሴት ምሁራን ጠየቁ

መቀሌ ፣ መጋቢት 09/2012 (ኢዜአ ) የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ በየደረጃው የሚገኙ ሴቶች ሲያደርጉት የነበረው ንቁ ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ የኢትዮጵያ ሴት ምሁራን ገለፁ።

በመቐለ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪና የኢንዱስትሪ ትስስር ማህበረሰብ አገልግሎት ግንኙነት ዳይሬክተር ዶክተር አለምፀሃይ ፀጋይ እንደተናገሩት ሴቶች የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታ እንዲጠናቀቅ የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርጉ ቆይተዋል።

በየደረጃው የሚገኙ ኢትዮጰያዊያን ሴቶች በእውቀታቸው ፣ በገንዘብና በጉልበታቸው የግድቡ ግንባታ ከዳር እንዲደርስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ዳይሬክተሯ አሳስበዋል።

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በአገሪቷ ኢኮኖሚ ትልቅ ለውጥ የማምጣት አቅም ያለው ፕሮጀክት መሆኑን በመገንዘብ ድጋፋችንን አጠናክረን መቀጠል አለብን ብለዋል።

በግድቡ ግንባታ ጉዳይ ላይ ለሶስቱ አገራት የቀረበው የስምምነት ሰነድ ኢትዮጵያን የሚጎዳ በመሆኑ መንግስት አልፈርምም ማለቱ ተገቢነት እንዳለውም ነው የገለጹት።

በተለይ "ሴት ምሁራን ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ ግንዛቤ ከመስጠት ጀምሮ  ተሳትፎአችን የጎላ መሆን አለበት " ብለዋል።

''ሴቶች አሁን ያለውን ወቅታዊ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ጉዳይ ተገንዝበው ሃሳብ በማመንጨት መንግስትን ማገዝ ይጠበቅባቸዋል ''ያሉት ደግሞ በመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ መምህርት የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር እልፍነሽ ይታገሱ ናቸው።

በአገር ጉዳይ የተሻለ ሀሳብ ማካፈል የሚችሉ ሴቶች እየተበራከቱ የመጡበት ወቅት ላይ እንገኛለን ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሯ ሴቶች በፕሮጀክቱ ቀጣይ እጣ ፈንታ ወሳኝ ሚና መጫወት እንደሚገባቸው አሳስበዋል ።

አሁን ተደጋግፈን ግድቡን ከመጨረስ ውጭ ሌላ አማራጭ የለንም  ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። 

በኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲ የስርአተ ፆታ ዳይሬክተር ወይዘሮ ዝምታ ኪዳኔ በበኩላቸው በግድቡ ግንባታ ላይ ሴቶች በብዛት እንዲሳተፉ ቢደረግ የበለጠ የመሳካት እድሉ ይሰፋል ብለዋል።

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው እውቀት፣ ገንዘብና ጉልበት ለመጨረስ በገቡት ቃል መሰረት ተባብረው መስራት አለባቸው ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም