ቀጥታ፡

በደብረ ብርሃን ከተማ የአልኮል እጥረት ተከስቷል

ደብረብርሃን  መጋቢት 9 ቀን 2012 ዓ.ም (ኢዜአ)  በደብረ ብርሃን ከተማ ለሕክምና አገልግሎት የሚዉል አልኮል በገበያ ላይ እጥረት በማጋጠሙ መቸገራቸውን የከተማው ነዋሪዎች ገለፁ።

ከኮሮና ቫይረስ መከሰት ጋር ተያይዞ ለሕክምና አገልግሎት የሚውል አልኮል በመድኃኒት ቤቶች ማግኘት እንዳልቻሉ የከተማው ነዋሪ የሆኑት አቶ መስፍን ጌቱ ለኢዜአ ገልጸዋል።

በዚህም የኮሮና ቫይረስንለመከላከል እጅን በአልኮል ለማጽዳት ችግር እንደገጠማቸው ጠቅሰው መንግሥት ተገቢውን ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ በፍጥነት እንዲቀርብ ጠይቀዋል።

ወይዘሮ ዓለምነሽ ምትኬ በበኩላቸው በከተማዋ በሚገኙ መድኃኒት ቤቶች የአልኮል አቅርቦት መጥፋቱን ጠቅሰዋል።

አንዳንድ ነጋዴዎች ለኮሮና ቫይረስ በሽታ መድኃኒት ይሆናል በሚል የተሳሳተ ወሬ አንድ ሎሚ እስከ 10 ብር፣አንድ የጠርሙስ ክዳንፌጦ ደግሞ እስከ 30 ብር እየተሸጠ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ለበሽታው መከላከል የሚያግዙ አልኮልና ሌሎች ቁሳቁሶች እንዲቀርቡ ከማድረግ ጎን ለጎን ተገቢው ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባ ወይዘሮ ዓለምነሽ አሳስበዋል።

ብራዘርስ የመድኃኒትና የሕክምና ዕቃዎች አቅራቢ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ትዕግስት ፋንታሁን በበኩላቸው ከሰሞኑ የአፍንጫና የአፍ ጭምብል እንዲሁም የአልኮል አቅርቦት እጥረት መከሰቱን ጠቅሰዋል።

አዲስ አበባ ከሚገኙ አምራች ድርጅቶች ጭምር የአቅርቦት እጥረት በመከሰቱ ማቅረብ እንዳልተቻለ ሥራ አስኪያጇ ጨምረው ተናግረዋል።

የአልኮል አቅርቦት እጥረት በመፈጠሩ ለመንግሥት ጤና ተቋማት መጠነኛ የአልኮል ምርት እንዲቀርብ ይደረጋል ያሉት ደግሞ የሰሜን ሸዋ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ፀዳለ ሰሙንጉሥ ናቸው።

የእጥረቱን ምንጭ ለመለየትና ተገቢውን የማስተካከያ እርምጃ ለማድረግ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በግል መድኃኒት ቤቶችና አከፋፋዮች ላይ ቁጥጥር ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

ኅብረተሰቡ የኮሮና ቫይረስን ሥርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የግልና የአካባቢ ንጽሕና መጠበቅ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ እንዳለበትም ወይዘሮ ፀዳለ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም