ቀጥታ፡

የአርሲና ራያ ዩኒቨርስቲዎች የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል እየሰሩ ነው

አሰላ/ማይጨው መጋቢት 9/2012/ኢዜአ/ የአርሲና የራያ ዩኒቨርስቲዎች የኮሮና ቫይረስን ስርጭትን ለመከላከል ኮሚቴዎችን አቋቁመው የተቀናጀ ስራ በማከናወን ላይ መሆናቸውን ገለፁ ።

የአርሲ ዩኒቨርሲቲ በሥሩ በሚገኙ የሶሻል ሣይንስና ሂዩማኒቲ ካምፓስ፣ በግብርና ኮሌጅ፣ በጤና ሣይንስና በዋና ቅጥር ጊቢ የተለያዩ ንዑስ ኮሚቴዎችን በማደራጀት እየሰራ ይገኛል።

በዩኒቨርሲቲው የዓለም አቀፍና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር ገመዳ ሁንዴ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት የበሽታውን ስርጭት ለመከላከልና ከተከሰተም ለመቆጣጠር የተማሪዎችን ግንዛቤ ከማሳደግ ጀምሮ የተለያዩ ሥራዎች እያከናወነ ነው ።

በተለይ ተማሪዎች የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ዘዴዎች በሣሙናና በአልኮል እጅ እንዲታጠቡ፣ ከንኪኪ ነፃ የሆነ ሠላምታ እንዲለዋወጡ የማስተማርና ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራዎች በአራቱም ካምፓሶች እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

ከአርሲ ዞን አስተዳደርና አሰላ ከተማ መስተዳድር ጋር በመቀናጀት ህዝብ በተሰበሰበበት ቦታ እጃቸውን በውሀና በሳሙና እንዲታጠቡ ፤አፍና አፍንጫቸውን  እንዲሸፍኑ የማስተማር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በህዝብ ትራንስፖርትና በመኖሪያ ቤት አካባቢ የሚደረጉ ጥንቃቄዎች ላይ ተማሪዎችና የግቢው ማህበረሰብ ትኩረት እንዲያደርግ  አስገንዝበዋል።

በአርሲ ዩኒቨርስቲ ከ13 ሺህ በላይ ተማሪዎች ትምህርት ላይ እንደሚገኙ ከዩኒቨርስቲው የተገኘው መረጃ ያሳያል።  

የራያ ዩኒቨርሲቲ በበኩሉ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።

የኮሮና ቫይረስ በዩኒቨርስቲው እንዳይከሰት አስቀድሞ የመከላከል ስራ እየተሰራ መሆኑን የዩኒቨርስቲው የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር መምህር ፅጋቡ ኃይለኪሮስ ተናግረዋል።

ቫይረሱን ለመከላከል ግብረ-ኃይል የተቋቋመ ሲሆን ፤ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች በአስቸኳይ እንዲሟሉ እና በተለያዩ መንገዶች ለተማሪዎችና ለዩኒቨርስቲው ሰራተኞች ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ተማሪዎች በመኝታ ክፍላቸው ውስጥ ተወስነው እንዲማሩ በተላለፈው መመሪያ መሰረት የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችን ተደራሽ በማድረግ ገንዘብ የሚያወጡበት የኤ ቲ ኤም ማሽን እና ሌሎች አገልግሎቶችም በግቢው ውስጥ የሚያገኙበት ሁኔታ የተመቻቸ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልፀዋል። 

ተማሪዎች የተሰጣቸውን የትምህርት መርጃ ዶክመንቶች በመኝታ ክፍላቸው ውስጥ ሆነው እንዲያጠኑ  እየተደረገ ነው ብለዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም