ቀጥታ፡

ኬንያ የግብፅን አቋም እንደምትደግፍ የተሰራጨው ዘገባ ሀሰት መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ መጋቢት 9/2012 (ኢዜአ) የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡኹሩ ኬንያታ አገራቸው በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የግብፅን አቋም እንደምትደግፍ በስልክ ለአብዱልፈታህ አልሲሲ ተናግረዋል በሚል የተሰራጨው ዘገባ ሀሰት መሆኑ ተገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኬንያ የኢትዮጵያ ባለ-ሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ ዓለምን ጠቅሶ እንደገለጸው በግብጽ የዜና አውታር የተገለጸው ዘገባ የተሳሳተ ነው።

አምባሳደር መለስ በኬንያ ለሚተላለፈው አሻም ቲቪ እንደገለጹት "አል-አህራም" የተሰኘው የግብጽ ጋዜጣ ኬንያ የግብጽን አቋም እንደምትደግፍ አድርጎ ያወጣው ዘገባ "የማደናገሪያ ፕሮፖጋንዳ ነው"።

የግብፅ ሚዲያዎች ከቀናት በፊት ጥቂት ግብፃውያን የተሰበሰቡበት ፎቶ በመለጠፍ "በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ግብፅን ደገፉ" በሚል የሀሰት ዜና ማሰራጨታቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

ግብፅ ባሳለፍናቸው ሳምንታት ድጋፍ ለማግኘት ስትል በግድቡ ላይ ያላትን አቋም ለተባበሩት አረብ ኢምሬቶች፣ ለሳዑዲ አረቢያ፣ ፈረንሳይ እና አውሮፓ ህብረት ስትገልፅ ቆይታለች፡፡

የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ በጉዳዩ ላይ የበለጠ ድጋፍ ለማግኘት በዚህ ሳምንት ወደ ተለያዩ የአፍሪካ አገራት የሚያደርጓቸውን ጉብኝቶች ጀምረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በበኩሏ በግድቡ ላይ ያላትን አቋም ለማስረዳት ወደተለያዩ አገራት የልዑካን ቡድኖች ልካለች፡፡

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ወደ ኬንያ አቅንተው ከኬንያው ፕሬዝዳንት ኡኹሩ ኬንያታ ጋር ውይይት ማድርጋቸው ይታወቃል።

በውይይቱም ፕሬዚዳንት ኡሁሩ የአባይን ወንዝ በተመለከተ ፍትሐዊና ምክንያታዊ ክፍፍል መኖር አለበት ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

ፕሬዝዳንቱ የአፍሪካዊያን አለመግባባቶች በአፍሪካዊያን መፈታት አለበት የሚል አቋም እንዳላቸውም አስታውቀዋል።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ከኬንያ በተጨማሪም ሩዋንዳና ኡጋንዳ በመጓዝ ከየአገራቱ ፕሬዝዳንቶች ጋር ተወያይተዋል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ኢትዮጵያ በግድቡ ላይ ያላትን አቋም ማስረዳታቸውና የአገራቱ መሪዎችም ለኢትዮጵያ ያላቸውን ድጋፍ መግለጻቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም