"ግብጽ በግድቡ ዙሪያ ለፍትሃዊ ተጠቃሚነት መርህ ቁርጠኛ መሆን አለባት" - ገዱ አንዳርጋቸው - ኢዜአ አማርኛ
"ግብጽ በግድቡ ዙሪያ ለፍትሃዊ ተጠቃሚነት መርህ ቁርጠኛ መሆን አለባት" - ገዱ አንዳርጋቸው
አዲስ አበባ መጋቢት 9/2012 (ኢዜአ) ግብጽ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ለፍትሃዊ ተጠቃሚነት መርህ ቁርጠኛ መሆን እንዳለባት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ገለጹ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከሰሞኑ ከሦስት ዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች ጋር ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ ኢትዮጵያ ግድቡን በተመለከተ አለመግባባቶችን ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።
ከቻይናው ዓለም አቀፍ ቴሌቪዥን (ሲጂቲኤን) ጋር ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ ኢትዮጵያ ዳግም ወደ ድርድር እንድትመለስ እውነተኛ ውይይት ያስፈልጋል ብለዋል።
ይህንን ለማድረግ ደግሞ ግብጽ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ሊኖራት እንደሚገባ ገልጸው የአባይ ውሃ የተፋሰሱ አገራት ውሃ መሆኑ ሊመራበት ይገባል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ውሃውን ብቻዋን መጠቀም የሚል ፍላጎትም ሆነ አስተሳሰብ እንደሌላት ገልጸው ነገር ግን በኃላፊነት የመጠቀም መብት እንዳላት በአግባቡ ትገነዘባለች ብለዋል።
የአረብ ሊግም በጉዳዩ ዙሪያ ምክክር ካደረገ በኋላ የግብጽን አቋም በመደገፍ መግለጫ ማውጣቱን ተከትሎ አቶ ገዱ የሚከተለውን ብለዋል።
“የአረብ ሊግም ይህን እድል በመጠቀም በአፍሪካ ቀንድና በመካከለኛው ምስራቅ መካከል መልካም ግንኙነት ለመፍጠር አዎንታዊ ሚና ሊጫወት ይገባል”።
በተመሳሳይ አቶ ገዱ ከአልጀዚራ ጋር ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ ኢትዮጵያ ግድቡን የምትገነባው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦቷን ለመጨመርና በተዘዋዋሪ ድህነቷን ለመዋጋት መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም ግብጽ ግድቡን በተመለከተ የምታካሂደውን የተሳሳተ አካሄድ በመተው ለእውነተኛ ድርድር መዘጋጀት አለባት፤ ግድቡ የፖለቲካ ጉዳይ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ግድቡን በሰባት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለመሙላት የወጠነች ሲሆን ግብጽ ደግሞ ከ12 እስከ 21 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የውሃ ሙሌት ሥራው እንዲከናወን ትፈልጋለች።
አቶ ገዱ ከአሜሪካው የዜና አውታር አሶሽየትድ ፕሬስ ጋር ባደረጉት ቆይታ ደግሞ በአሜሪካ በነበረው የሦስትዮሽ ውይይት ዋና ዋና ጉዳዮች እልባት ሳይሰጣቸው ኢትዮጵያ ሥምምነቱን እንድትፈጽም ይፈለግ እንደነበር ያወሳሉ።
ኢትዮጵያ በማንም ጫና ግድቡን በተመለከተ ምንም አይነት ሥምምነት አትፈጽምም ሦስቱ አገራት ልዩነታቸውን ያለምንም ሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት መፈጸም አለባቸው ሲሉም ተናግረዋል።
በችኮላ የሚፈጸም ሥምምነት ለየትኛውም ወገን እንደማይጠቅም ጭምር ነው አቶ ገዱ በቃለ-መጠይቁ ያሰመሩበት።
ኢትዮጵያ አሜሪካ በታዛቢነት በዋሺንግተን እየተካሄደ በነበረው የሱዳን፣ የኢትዮጵያና የግብጽ የሦስትዮሽ ሰብሰባ የመጨረሻውን አለመሳተፏ ይታወቃል።
ይህን ተከትሎም ግብጽ የኢትዮጵያን አለመሳተፍ አግባብነት አንደሌለው ገልጻ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር ማንኛውንም መንገድ እንደምትከተል በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቷ በኩል ገልጻለች።
አቶ ገዱ ለአሶሽየትድ ፕሬስ እንደተናገሩት፤ ግድቡን በተመለከተ የሚነሱ አለመግባባቶችን ለመፍታት ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የራሷን መፍትሄ እያዘጋጀች ሲሆን በቅርቡም ለግብጽና ለሱዳን ይቀርባል።
6 ነጥብ 4 ጊጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ71 ነጥብ 59 በመቶ ደርሷል።