ቀጥታ፡

ግንባታው በስምንት ወር ይጠናቀቃል የተባለው የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ከስምንት ዓመት በኋላም ስራ አልጀመረም

አዲስ አበባ መጋቢት 9/2012 (ኢዜአ) በስምንት ወር ይጠናቀቃል ተብሎ የተጀመረው የአፋር ሱኑታ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ከስምንት ዓመታት በኋላም አገልግሎት መስጠት አልቻለም።
የመስኖ ፕሮጀክቱ በ2004 ዓ.ም በፌዴራል መንግስት በተመደበ ከ691 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ነው የተጀመረው።

በፕሮጀክቱ 50 የሚሆኑ ከ200 እስከ 300 ሜትር ጥልቀት ያላቸው ጉድጓዶችን ተቆፍረው ለስራው ዝግጁ ተደርገው እንደነበርም ተገልጿል።

በ2008 ዓ.ም ስራው 98 በመቶ መጠናቀቁ ቢገለጽም ከሶስት ዓመት በኋላ ደግሞ በርካታ የፕሮጀክቱ እቃዎች በሌቦች ተዘርፈዋል።

ፕሮጀክቱን በድጋሚ ለማስጀመርም ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ ወጪ ጠይቋል ነው የተባለው።

በዚህ ሳቢያ ከስምንት ዓመት በፊት ከ5 ሺህ የሚልቁ የአካባቢውን አባወራዎች ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመረው ፕሮጀክት እስካሁን አገልግሎት መስጠት አልቻለም።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ካባ ኡርጌሳ ለኢዜአ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ በአሰሪው ተቋም ተጠናቆ በ2008 ዓ.ም የርክክብ እንፈጽም ጥያቄ መቅረቡን አስታውሰዋል።

ሆኖም ፕሮጀክቱ በአግባቡ መጠናቀቁን አጣርቶ ለመረከብ በወቅቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ባለመግባቱ መረካከብ ሳይቻል ሶስት ዓመታት ተቆጥረዋል።

ዘግይቶም ቢሆን የኤሌክትሪክ ኃይል ገብቶ ለርክክብ ወደ ስፍራው ሲኬድም በርካታ የፕሮጀክቱ አካላት በህገ-ወጦች ተዘርፈዋል ነው ያሉት ዶክተር ካባ።

በ2011 ዓ.ም መጨረሻ በተደረገ ጥናትም ፕሮጀክቱን ለማስጀመር ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ ወጪ ጠይቋል ብለዋል።

ዶክተር ካባ ፕሮጀክቱ መጀመሪያም በአግባቡ ጥናት ተደርጎበትና የአካባቢውን ነዋሪዎች አሳምኖ ያልተገባበት መሆኑ ለችግሩ እንደ ምክንያት ሊጠቀስ ይችላል ነው ያሉት።

ዕቅዱም ቢሆን በጥናት ላይ ያልተመሰረተ፣ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ፣ ፍላጎትና አቅም ያላገናዘበ ነበር ብለዋል።

በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የሠላም ሚኒስትር አማካሪ አቶ ካይዳጊ ገዛኸኝ ፕሮጀክቱ ከተፋስስ ልማት ጋር ተያይዞ በመስኖ ልማት፣ በመጠጥ ውሃ አቅርቦትና በአጠቃላይ የአካባቢውን አቅም ለመገንባት የተጀመረ ነው ይላሉ።

ክልሉን በዘላቂነት ወደ ልማት ለማስገባት በማሰብ ከፌዴራልና ከክልል እንዲሁም ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከሜቴክና ከሌሎች አገር በቀል ድርጅቶች ጋር ስምምነት በመፈራረም ነው የተጀመረው።

ግንባታው አርብቶ አደሩን ከተበታተነ የአኗኗር ዘይቤ በአንድ አካባቢ እንዲረጋጋ በማድረግ ለህብረተሰቡ የትምህር፣ የጤናና ሌሎች ግልጋሎቶችን በቅርበት ለማዳረስ ያለመ እንደነበርም አውስተዋል።

ነገር ግን ፕሮጀክቱ ተጠናቆ የአካባቢውን ህብረተሰብ ችግር በዘላቂነት እየፈታ ባለመሆኑ የመንግስት ውሳኔ ታክሎበት ዘላቂ መፍትሄ ያሻዋል ነው ያሉት።

በግብርና ሚኒስቴር የዘላቂ ልማት ግቦች ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢንጂነር አድናን አህመድ ፕሮጀክቱ በ2008 ዓ.ም ተጠናቆ የሙከራ ስራ ጀምሮ ውጤቱም አመርቂ እንደነበር ጠቅሰዋል።

ግንባታው በስምንት ወር እንደሚጠናቀቅ ታቅዶ በስምንት ዓመት ቢጠናቀቅም በኃይል እጥረት ቀጣይነቱ ሳይረጋገጥ ቀርቷል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ተጠናቆ ቢሆን አምስት ሺህ አባወራዎች በዓመት ሁለትና ሶስት ጊዜ በማምረት ኑሯቸውን ማሻሻል ይችሉ ነበር።

ፕሮጀክቶች ለሕዝብ ቃል ተገብቶ ወደ ስራ ሲገቡ በተለያዘላቸው የጊዜ ገደብ ካልተጠናቀቁ እምነት ያሳጣል ነው ያሉት።

የአፋር ክልል መንግስት ፕሮጀክቶችን በመከፋፈል ወደ ስራ ለማስገባት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ኃላፊው ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም