የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት 12ኛ መደበኛ ጉባኤውን ከሰኞ ጀምሮ ያካሂዳል

52
መቀሌ ሰኔ 22/2010 የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አምስተኛ ዘመን 12ኛ መደበኛ ጉባኤውን ከመጪው ሰኞ ጀምሮ እንደሚያካሂድ አስታወቀ። የምክር ቤቱ የኮንፈረንስና የህዝብ ግኑኝነት ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ ታረቀ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት ምክር ቤቱ ጉባኤውን ከሰኞ ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ያካሂዳል። ምክር ቤቱ በጉባኤው የምክር ቤቱንና የክልሉ ሥራ አስፈጻሚ አካላት የ2010 በጀት ዓመት የሥራ ዕቅድና አፈጻጸም ሪፖርትን በማዳመጥ ውይይት ያደርጋል። በተጨማሪም ተጠሪነታቸው ለምክር ቤቱ የሆኑትን የክልሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ የዋና ኦዲተርና የትግራይ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ በበጀት ዓመቱ ያከናወኗቸውን ሥራዎች አስመልክቶ በሚያቀርቡት ሪፖርት ላይ አባላቱ ውይይት እንደሚያደርጉ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪ በ2011ዓ.ም በክልሉ ለሚከናወኑ ሥራዎች በሚውል የበጀት ረቂቅ አዋጅ ላይ የምክር ቤቱ አባላት ተወያይተው ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል። እንዲሁም  በሌሎች ሁለት አዋጆች ላይ ተመሳሳይ ውይይት በማድረግ ምክር ቤቱ ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም