ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ 22 መድሃኒት ቤቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ

አዲስ አበባ መጋቢት 9/2012 (ኢዜአ) በመዲናዋ በ230 መድሃኒት ቤቶችና መድሃኒት መደብሮች ላይ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ 22ቱ ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ በማድረጋቸው እርምጃ የተወሰደባቸው መሆኑን የአዲስ አበባ ምግብ መድሃኒት ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ። 

የኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ ስርጭቱን ለመከላከል የሚያግዙ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ላይ ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ በመኖራቸው ባለስልጣኑ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ፋርማሲዎችና መድሃኒት መደብሮች ላይ ድንገተኛ ቁጥጥር አካሂዷል፡፡

ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሰረት መጋቢት 7 እና 8 ቀን 2012 ዓ.ም ብቻ በ230 መድሃኒት ቤቶችና መደብሮች ላይ ድንገተኛ ፍተሻ ተከናውኗል።

በቁጥጥሩ ሂደትም 7 ተቋማት የፁሁፍ ማስጠንቀቂ ሲሰጣቸው 15 ተቋማት እንዲታሸጉ መደረጉን ከባከስልጣኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በተያያዘ ዜና በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ዶቼ ክሊኒክ ጀርባ በአንድ የውኃ ማሸጊያ ፕላስቲክ (ሃይላንድ) ክዳን ፌጦ በ10 ብር ስትሸጥ የተገኘች ግለሰብ በሕዝብ ጥቆማ መያዟ ታውቋል።

ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ሲሸጡ የነበሩ 37 የበርበሬ መሸጫ ሱቆች መታሸጋቸውንም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ይፋ እድርጓል።

በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 በርበሬ በረንዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በኪሎ 90 ብር ይሸጥ የነበረውን በርበሬ በ180 ብር እንዲሁም አንድ ኪሎ ነጭ ሽንኩርት በ300 ሲሸጡ የተደረሰባቸው 37 የንግድ ሱቆች ናቸው የታሸጉት።

ከዚህ በተጨማሪም ደረጃውን ያልጠበቀ የፊት መሸፈኛ ማስክ በተጋነነ ዋጋ ሲሸጡ የተገኙ 4 ግለሰቦች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል።

በቀጣይም ተመሳሳይ ተግባር በሚፈፅሙ ነጋደዎች ላይ የተጠናከረ እርምጃ እንደሚወስድ ኮሚሽኑ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም