የኮሙኒኬሽን ባለሞያዎች ስለ ኮሮና ቫይረስ ትክክለኛ መረጃ ማድረስ ይጠበቅባቸዋል --ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ - ኢዜአ አማርኛ
የኮሙኒኬሽን ባለሞያዎች ስለ ኮሮና ቫይረስ ትክክለኛ መረጃ ማድረስ ይጠበቅባቸዋል --ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ
መጋቢት 8/2012 (ኢዜአ) የኮሮና ቫይረስን ለመከላከልና ሥርጭቱን ለመግታት የኮሙኒኬሽን ባለሞያዎች ትክክለኛ መረጃ በማስተላለፍ ኅብረተሰቡን የማረጋጋት ሚናቸውን እንዲወጡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አሳሰቡ።
ኅብረተሰቡ ስለ ቫይረሱ ትክክለኛ መረጃ ማግኘት ስለሚችልበት ሁኔታ የፌዴራልና የክልል ኮሙኒኬሽን ኃላፊዎችና የጤና ቢሮዎች ኮሙኒኬሽን ባለሞያዎችን ያሳተፈ ውይይት ዛሬ ተካሂዷል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በተካሄደው ውይይት በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚመጡ ሀሰተኛ መረጃዎች ኅብረተሰቡ ላይ ጫና እያሳደሩ መሆናቸው ተገልጿል።
የኮሙኒኬሽን ባለሞያዎች ሀሰተኛ መረጃዎች በኅብረተሰቡ ውስጥ እየፈጠሩት ያለውን ስጋትና መደናገጥ ተረድተው በማምከን ትክክለኛ መረጃ መስጠት እንደሚገባቸው ተገልጿል።
በመድረኩ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አሁን ካጋጠመው፣ ከዚህ ቀደሙና ወደፊትም ሊያገጥም ከሚችለው ችግር ማኅበረሰቡን እንዴት ማንቃት አለብን በሚለው ጉዳይ ላይ ባለሙያዎቹ ግንዛቤ ሊይዙ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ የሚለቀቁ ሀሰተኛ መረጃዎች በኅብረተሰቡ ውስጥ ድንጋጤን ይፈጥራሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም በአገራት ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ላይ ከሚደረጉ ጥቃቶች አንዱ ነው ብለዋል።
በአራት መንገዶች ጥቃት ሊሰነዘር ይችላል ያሉት ዶክተር አብይ ፊዚካል፣ ሎጀስቲክ፣ የኢንፎርሜሽንና የሂውማን ሌቭል ጥቃት የሚሉ ጉዳዮችን ለአብነት አንስተዋል።
እነዚህ ጥቃቶች የአገርን ህልውና የሚገዳደሩ ቢሆኑም የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች እነዚህን ሁኔታዎች የመቀየር ሚና እንዳላቸው ጠቅሰዋል።
ባለሙያዎች ምን አይነት መረጃ ከየት መጣ የሚለውን በማጥራት ኅብረተሰቡ በቀላሉ ሊረዳው በሚችል ቋንቋ ማድረስ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።
ስለ ቫይረሱ የሚሰራጭ ከልክ ያለፈ ግነትና ቅለት ተገቢ ያለመሆኑን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ትክክለኛ መረጃ በመያዝ የሚያስፈልገውንና የሚጠቅመውን ለኅብረተሰቡ ማድረስ እንደሚገባቸው ገልፀዋል።
ቻይና ጠንካራ የኮሙኒኬሽን ስርዓት በመገንባቷ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን በመግታት ሌሎች ኃያላን አገራትን እያገዘች እንደምትገኝ ጠቅሰዋል።
የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎችም በእውቀትና በጥበብ በመራመድ ኢትዮጵያን ከዚህ ወረርሽኝ ተከላክለው ሌሎች አፍሪካዊያን ወንድሞችን ለማገዝ መስራት እንደሚገባቸው ነው የተናገሩት።
በተደመረ አስተሳሰብና አሰራር ኢትዮጵያዊያን ትክክለኛ መረጃ ሊያገኙ በሚችሉበት ሁኔታ የኮሙኒኬሽን ባለሞያዎች ትክክለኛ መረጃዎችን በማስተላለፍ የማረጋጋት ሚናቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው ወረርሽኙ ከተሰማ ጀምሮ ለመከላከል በፌዴራልና በክልሎች መካከል ሲሰሩ የነበሩ የቅንጅት ስራዎችን አብራርተዋል።
ቦሌ አየር ማረፊያን ጨምሮ 30 በሚሆኑ የየብስ በሮች እንዲሁም በበሽታው የተጠረጠሩ ሰዎችን ለይቶ ማቆየትን ጨምሮ የተቋቋመው ብሄራዊ ግብር ኃይልና ኮሚቴ እየሰራ ያለውን ስራ አብራርተዋል።
በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ በአዲስ አበባ ሙሉ ምርመራና የማረጋገጫ ስራ እየተሰራ ስለመሆኑ ጠቅሰው ይህንኑ ወደ ክልል የማስፋት ስራ እንደሚሰራም አክለዋል።
እስካሁን አምስት ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን፤ ከእነርሱ ጋር ግንኙነት የነበራቸው ሰዎችም በለይቶ ማቆያ ክትትል እየተደረገላቸው ስለመሆኑ ተናግረዋል።
የኮሙኒኬሽን ባለሞያዎች የሚሰጡት መረጃ ትክክለኛና ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ሊሆን እንደሚገባም አስገንዝበዋል።