የሃይማኖት አባቶች ግጭቶችን ለመከላከል ጠንክረው መስራት አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
የሃይማኖት አባቶች ግጭቶችን ለመከላከል ጠንክረው መስራት አለባቸው
ባህር ዳር፤ መጋቢት 8/2012 (ኢዜአ) ተከባብሮ በኖረው ህዝብ መካከል በሃይማኖት ሰበብ የሚነሱ ግጭቶችን በመከላከል መቻቻልን ለማስፈን የሃይማኖት አባቶች ጠንክረው መሰራት እንዳለባቸው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ አሳሰቡ።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ከሃይማኖት ተቋማት አመራሮች ጋር በባህር ዳር ከተማ ዛሬ ተወያይተዋል።
ርዕሰ መስተዳደሩ እንደገለጹት በኢትዮጵያ የተለያዩ የእምነት ተከታዮች ተከባብረው ለዘመናት ኖረዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የህዝቡን ተቻችሎ መኖርና የህዝቦች አንድነት የማይመቻቸው አካላት ህዝቡን ለመለያየት አልሳካ ሲላቸው እምነትን ስበብ በማድረግ ችግር እየፈጠሩ ይገኛል።
ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የእምነት ተቋማትን የማቃጠልና ህዝቡ በእምነት ምክንያት እርስ በርሱ እንዲጠራጠር የማድረግ ስራዎች ተሰርተዋል። አሁንም እየተሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም የአማራ ህዝብ አንዱ የአንዱን የእምነት ቦታ ተባብሮ እየገነባና ተማምኖ የኖረ ህዝብ መሆኑን አመልክተዋል።
የእምነት ተቋማት መስሪያ ቦታና የመቃብር ስፍራዎችም የቅሬታ ምንጮች እየሆኑ መምጣታቸውን ገልፀው ይህንንም "አንተ ትብስ አንተ ትብስ" በሚል የተለመደ ኢትዮጵያዊ ባህል መፍታት ሲገባ አላስፈላጊ ቅሬታ ውስጥ መገባት የለበትም ብለዋል።
በክልሉ ውስጥ በርካታ እምነቶች እንዳሉ የገለፁት ርእሰ መስተዳድሩ መንግስት ሁሉንም በእኩል ዐይን በማየት ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ይሰጣል።
የህግ የበላይነትን እንዲከበር የሃይማኖት አባቶች ተከታዮቻቸውን በማስተማር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለባቸው አቶ ተመስገን አሳስበዋል።
የክልሉ መንግስት የሚስተዋሉ የህገ-ወጥነት እንቅስቃሴዎችን ለመግታት መጠነ-ሰፊ ስራዎችን እያከናወነ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ ለዚህ ደግሞ የሃይማኖት አባቶች ምዕምናኑን በማስተማር ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል ።
"ኢትዮጵያዊያን የራሳቸውን እምነት አጥብቀው የሌሎችን ሲያከበሩ የሚኖሩ ህዝቦች በመሆናቸው የአለም ምሳሌዎች ናቸው" ያሉት ደግሞ የባህርዳር ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጽዑ አቡነ አብረሃም ናቸው።
በመሆኑም ህዝቡ እምነቱን ምክንያት በማድረግ እርስ በእርሱ ሊያጋጩት ከሚያቋምጡ አካላት እራሱን ሊያርቅ እንደሚገባ መክረዋል ።
ኢትዮጵያዊያን የአንዱ የእምነት ተቋም ሲሰራ ሌላው ገንዘብ በማዋጣትና በጉልበት በመተባበር ሲደጋገፉ ለረጅም ዘመናት የኖሩ መሆናቸውንም አመልክተዋል።
አሁን የእምነቶችን አላማ ያልተረዱ አካላት ልዩነት ለመፍጠር እየሰሩ ስለሆነ ህዝቡ ነቅቶ ሊጠብቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በእምነቶች መካከል ልዩነትና ግጭት በመፍጠር ሊጠቀሙ የሚጥሩ አካላት የየትኛውንም እምነትና ተቋም ስለማይወክሉ ህዝቡ ነቅቶ ሊጠብቃቸው ይገባል ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሰዒድ መሀመድ ናቸው።
በውይይት መድረኩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና የተለያዩ ሃይማኖት አባቶችና ተወካዮች ተገኝተዋል።